➯…የኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ወደ ሀገር ቤት
ተመልሷል…
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር 23ኛ ሳምንት መርሃግብር ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን ባልተጠበቀ መልኩ 4ለ3 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል።
በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለያየ ወቅት የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ የሆኑት አቡበከር ናስርና ጌታነህ ከበደ ለየክለባቸው ሁለት ሁለት ግብ በማስቆጠር በ11 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነት ፉክክሩን ከእስማኤል ኦሮ አጎሮ እጅ በመንጠቅ ሀገራዊ መልክ አስይዘውታል።
ለወልቂጤ ጫላ ተሺታ በ12 ሰከንድ ሪከርድ በሆነ መልኩ ሲያስቆጥር የኢትዮጵያ ቡናን ቀሪ ግቦች የአብቃል ፈረጃና አስራት ቱንጆ ከመረብ አሳርፈዋል። 2ለ0..2ለ1..3ለ1.. 3ለ3…በመጨረሻም ዳኛው የጨዋታውን ማጠናቀቂያ ፊሽካ ሲነፋ ቡናማዎቹ ክትፎዎቹን 4ለ3 ያሸነፉበት ጨዋታ ሆኗል።ቡናዎቹ ላስመዘገቡት ድል ጫላ ተሺታ ለጌታነህ ከበደ ያቀበላቸው የመጨረሻ ወሳኝ ኳሶች በተገቢው መንገድ ያልተላኩ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ቡናን 5 ለ 1 እንዳይመራና በስተመጨረሻ እንዲያሸንፍ አግዘውታል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ሂደት አቡበከር ናስር በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በወልቂጤ ከተማው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንኮራ ፋውል ቢሰራበትም አርቢትሩ ሳያዩት ቀርተዋል ከግቡ ኋላ የነበረው ተጨማሪው አርቢትር ማንደፍሮ አበበም ከሃላፊነቱ ውጪ በመሆኑ ዳኛውን ሳያግዘው ቀርቷል።
የማይከፈላቸው ወይም አበል የማይታሰብላቸው ከግብ ኋላ ያሉት ዳኞች ሀላፊነት መገደቡ አነጋጋሪ ሆኗል። ዳኞቹ 16 ከ 50 ውስጥ የሚፈጠር የመሃልና ረዳት ዳኞች ያላዩትን የመጠቆም መብት ካልተሰጣቸው ከስንት አንዴ ሊፈጸም የሚችለውን መስመር አለፈ የሚለውን ለመናገር ብቻ መመደባቸው ለውጥ የሌለው በመሆኑ ሊግ ኩባንያው ከብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ሊያስተካክለው እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቡ እየጠየቀ ነው።
ሊጠናቀቅ የ7 ሳምንት ጨዋታ በቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክብረወሰኑን በነጠቀው አቡበከር ናስርና ሪከርዱን በተቀማው ጌታነህ ከበደ መሃል ያለው የእርስ በርስ ፍልሚያ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ጋር ያለው ትንቅንቅ ከዋንጫው ላለመውረድ ከሚደረገውና ሁለተኛ ሆኖ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ ለመሆን ከሚደረገው ፍልሚያ ጋር ተጨምሮ ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ትኩረት ያገኙ ሆነዋል።
ዛሬ ጠዋት በተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስና የወላይታ ድቻ ጨዋታም ያለግብ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ፈረሰኞቹ ደከም ባሉበት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በርትተው የገቡበትን ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ በመሃል ዳኝነት መርቶታል። በዚህ ጨዋታ የፈረሰኞቹ የመሃል ሜዳ ኮከብ ከነዓን ማርክነህ ትከሻውን ተጎድቶ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። ውጤቱን ተከትሎ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ማጠናከር ሳይችሉ ቀርተው ሁለት ውድ ነጥቦችን ጥለዋል። ነገ ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ ልዩነቱ ወደ 8 ነጥብ የሚጠብ መሆኑ ጨዋታውን የበለጠ ተጠባቂ አድርጎታል።
ሊጉ ነገ ሲቀጥል ከጠዋቱ 4 ሰአት ሲዳማ ቡና ከመከላከያ 7 ሰአት ሀዋሳ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ 10 ሰአት ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ 23ኛው ሳምንት ይጠናቀቃል ብሎ ይጠበቃል።