የባህርዳር ከተማዉ ተጫዋች ግርማ ዲሳሳ የ4 ጨዋታ እንዲሁም የክለብ አጋሩ አህመድ ረሽድ (ሽሪላዉ) የ3 ጨዋታ ቀጣት ተጥሎባቸዋል ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ የካቲት 12 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚህም በተጫዋቾች ግርማ ዲሳሳ(ባህር ዳር ከተማ) በከባድ የአጨዋወት ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን 4 ጨዋታ እንዲታገድ እና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት 4000 እንዲከፍል ተወስኗል።
በተጨማሪም ግጥሚያ ከተጠናቀቀ በኋላ ዳኛን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው እና በፀጥታ አካላት ከሜዳ ስለመውጣታቸው ሪፖርት የተደረገባቸው አህመድ ረሽድ(ባህር ዳር – በእለቱ ጨዋታ ያልተመዘገበ የክለቡ ተጫዋች) 3 ጨዋታ እንዲቀጣና ተጨማሪ 3000 ብር እንዲከፍል እንዲሁም የክለቡ የቡድን መሪ አቶ ሄኖክ ሀብቴ ስድስት ጨዋታ እንዲቀጡና ተጨማሪ 5000 ብር እንዲከፍል ተወሰኗል።
- ማሰታውቂያ -
በክለብ ደረጃ መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማ የክለቦቹ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
ከተጫዋቾች ውስጥም አምስት ቢጫ ካርድ በማየት በቀጣይ ጨዋታ የማይሰለፉት ቃልኪዳን ዘላለም ከወላይታ ዲቻ ፣ በረከት ወ/ዮሀንስ ከወላይታ ድቻ እና ጊት ጋትኩት ከሲዳማ ቡና መሆናቸው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አሳውቋል።