ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ከመከላከያ ጋር ባደረገዉ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታ 4ለ0 መሸነፉ የሚታወስ ነው። ይህ ጨዋታ በሚከናወንበት ግዜ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የቡድናቸውን አመራሮች እና አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ግዜ አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው ምክንያት ክለቡ 100,000 ብር እንዲከፍልና እንዲሁም ከድሬደዋ ከተማና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ባህር ዳር ላይ የሚያደርጋቸውን ቀጣይ 2 ጨዋታዎች ያለደጋፊ በዝግ ስታድየም እንዲያደርግ መወሰኑን ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት የፕሪሚየር ሊጉ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች የውድድር አመራሮችን ስለመሳደባቸው ሪፖርት ስለቀረበባቸው የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ከፈፀሙት ጥፋትና ድርጊት ባሻገር ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጥፋት ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ምክንያት አዳማ ከተማ 75000 ብር እንዲከፍል መወሰኑን ሊግ ካምፓኒው አስታውቋል።
በሌላ በኩል ሰበታ ከተማ ከድሬደዋ ከተማ ጋር ባደረገዉ ጨዋታ የሰበታ ከተማ ደጋፊዎች የውድድር አመራሮችን ስለመሳደባቸው በተመሳሳይ ሪፖርት የቀረበበት በመሆኑ የክለቡ ደጋፊዎች በፈፀሙት ጥፋት ሳቢያ ክለቡ 50000 ብር እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል ሲል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታዉቋል።
በተጫዋቾች ደረጃ ያሲን ጀማል ፣ መሐመድ ኑር ናስር ፣ መድሀኔ ብርሀኔ ፣ ሮቤል ተ/ሚካኤል ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ከድር ኩሊባሊ በአምስት ቢጫ ምክንያት አንድ ጨዋታ ሲታገዱ በተጨማሪም የ1500 ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።