በታሪካዊ ክሰተቶች ታጅቦ የተጀመረው የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ የ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ፕሮቶኮልን ጠብቆ በሀገሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ የቀጥታ ሽፋንን በማግኘት በ ሱፐር ስፖርት መተላለፍን ከጀመረ ወራትን ሊያስቆጥር የሳምንታት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል ።
የመጀመሪያው ዙር የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በ አዲስ አበባ ስታዲየም ፣ በ ጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እና በ ባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም እንዲካሄዱ የወጣው መርሀ ግብር ሲያሳይ የመጀመሪያው ስድስት ሳምንታት ጨዋታዎችን የአዲስ አበባ ስታዲየም አካሂዶ ጨርሷል ። ሰላሳ አራት ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋንን ሲያገኙ በሀገሪቱ የሰሜን ክፍል በነበረው ፖለቲካዊው አለመረጋጋት የ 2011 የሊጉ ሻምፒዮንን መቐለ 70 እንደርታ ጨምሮ ሁለቱ የሰሜን ክልል ክለቦች ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በሊጉ ሳይሳተፉ ቀርተዋል ። ጅማሮውን ካደረገ ወራትን ሊያስቆጥረው የተቃረበው የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በርካታ ሁነቶችን ሲያሳይ የነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎችን ጨምሮ የወሩ ምርጥ ተጫዋችን እንደሚከተለው ይቀርባል ።
በመጀመሪያዎቹ ስድስት ሳምንታት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ 36 ጨዋታዎች 107 ጎሎች ከመረብ ሲያርፉ የወላይታ ድቻው የመሀል ሜዳ ተጫዋች እድሪስ ሲዒድ 50ኛውን እንዲሁም የቡድን አጋሩ አማኑኤል ተሾመ 100ኛውን የሊጉን ጎል ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል ። ይህም በባለፈው የውድድር ዓመት በአስራ ስድስት ክለቦች ከተካሄደው የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ጋር በአራት ግቦች ከፍ ብሎ ይታያል ።
- ማሰታውቂያ -
ከባለፈው የውድድር ዓመት ሲነፃፃር ለተመልካች አዝናኝ በነበረው የስድስቱ ሳምንታት የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በሶስት የጨዋታ መርሀ ግብሮች ብቻ ግብ ሳይሰተናገድ የአቻ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል ። በአማካይ ሲሰላ የዘንድሮው የውድድር ዓመት በጨዋታ 2.97 ጎሎች ይቆጠራሉ ።
አጫጭር እውነታዎች •
በሊጉ ከተቆጠሩ 107 ጎሎች ላይ በ 59ኝ ተጫዋቾች ሲቆጠሩ ሶስቱ በራስ ግብ ላይ የተቆጠሩ ሆነው አልፈዋል ።
ኢትዮጵያ ቡና በተጋጣሚዎች ላይ ብዙ ጎሎችን ያስቆጠረ ክለብ ሲሆን አስራ አራት ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል ።
የሊጉ መሪ ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ ምንም ጨዋታዎችን ያልተሸነፈው ብቸኛው ክለብ ነው ።
ጅማ አባ ጅፋር ምንም ጨዋታ ያለሸነፈው የሊጉ ብቸኛ ክለብ ሲሆን በተቃራኒው ወላይታ ድቻ ብዙ ጨዋታዎችን አምስት የተሸነፈው ክለብ ነው ።
በታሪካዊው አዲስ አበባ ስታዲየም የኮሮና ቫይረስ ፕሮቶኮልን ጠብቆ በተካሄደው የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በርካታ ካርዶች ሲመዘዙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ባሳዩት ከስፖርታዊ ውጪ በሆነ ተግባር መሆኑ አስገራሚ ሆኖ አልፏል ። 120 የቢጫ ካርዶች ሲመዘዙ 72 የሚሆኑት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ ተጫዋቾች ባሳዩት ተግባር ሲመለከቱ አስር የቀይ ካርዶች ተመዘዋል ። ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ጨዋታዎች ጋር ሲተያይ ዝቀተኛ ቁጥርን ( 164 የቢጫ ካርዶች ) የተመለከትንበት ሆኗል።
በርካታ ተጫዋቾች የግል ብቃታቸውን ባሳዩበት ስድስት ሳምንታት በከፍተኛ ግብ አግቢነቱ የተፋጠጡት አቡበከር ናስር ( ኢትዮጵያ ቡና ) እና ሙጂብ ቃሲም ( ፋሲል ከነማ ) ብቸኞቹ ሀትሪክ ሰሪዎች ሆነው አልፈዋል ። የአፄዎቹ የፊት መስመር አጥቂ ሙጂብ ቃሲም በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥሙ ብቻ ግብ ሳያስቆጥር ሲቀር በተቀሩት ሳምንታት ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
ሁለት ተጫዋቾች ከዚህ ባለፈም በስድስት ሳምንታት ጉዞ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ የፊት መስመር አጥቂ እና አምበል ጌታነህ ከበደ ጋር በመሆን በሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ቡድናቸውን በአሸናፊነቱ ሲያስገሰግሱ ታይተዋል ። ከሶስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪም ሀብታሙ ታደሰ ፣ ያሬድ ታደሰ ፣ ታፈሰ ሰርካ ፣ አብዲሳ ጀማል ፣ ስንታየሁ መንግስቱ እንዲሁም ፍፁም አለሙ በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው ።አይቮሪኮስታዊው የሊጉ መሪ ሀድያ ሆሳዕና ተጫዋች ሳሊፍ ፎፎና ብቸኛው ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለ የውጭ ሀገር ተጫዋች ለመሆን ችሏል ።
ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበሉ ረገድ ትልቅ ድርሻን የተወጡ ተጫዋቾች ሲኖሩ በተለይም የቅዱስ ጊዪርጊሱ ኮከብ አቤል ያለው በአንድ ጨዋታ አመቻችቶ በማቀበል ሀትሪክ መስራት የቻለ ብቸኛው ተጫዋች ለመሆን ችሏል ። እርሱን በመከተል እዮብ ማቲያስ ፣ አስራት ቱንጆ ፣ ሽመክት ጉግሳ በአንድ ጨዋታ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ቀዳሚውን ተከታዩን ስፍራ ይይዛሉ ። በዚህ ረገድ ጋናዊው በሊጉ ልምድ ያለው የሀድያ ሆሳዕና የመሐል ክፍል ተጫዋች ካሉሻ አልሀሰን በተመሳሳይ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ብቸኛው የውጭ ሀገር ተጫዋች ነው ። ግብ በማስቆጠር እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በድምሩ የኢትዮጵያ ቡናው ኮከብ አቡበከር ናስር በዘጠኝ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎን በማድረግ ይመራል ። ተከታዩን ደረጃ የያዙ ተጫዋቾች ከስር በምስሉ ላይ ተገልፀዋል ።
በዘንድሮው ፕርሚየር ሊግ ላይ የግብ ጠባቂዎች ተሳትፎ ለጎሎች መቆጠር ጉልህ ሚናን ተጫውቶ ሲያልፍ የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል እና የሀድያ ሆሳዕናው ደረጄ አለሙ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችተው ማቀበል የቻሉ ግብ ጠባቂዎች ሆነው በስድስቱ ሳምንት የሊጉ ጉዞ አልፈዋል ። ይህ ክስተት በዘንድሮው የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግበፈጣኑ ሲሆን በተቋረጠው የባለፈው የውድድር ዓመት ይህን ክስተት ለማየት የሁለተኛው ዙር የውድድር ጊዜን መጠበቅ ግድ ሲል የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ደግሞ ይህን ያደረገው ብቸኛው ተጫዋች ነበር ።
በዘንድሮው የ ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ጥሩ አቅም ያላቸውን ድንቅ ወጣት ተጫዋቾችን መመልከት ስንችል በተለይም የወልቂጤ ከተማው ተስፈኛ ያሬድ ታደሰ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑን ሲታደግ ተስተውሏል ። ሌላኛው ወጣት ተጫዋች ያለፉትን አመታት በተለይም ለውጭ ሀገር ግብ ጠባቂዎች እድል መስጠትን እንደ ባህል በሚታይበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታግሎ በመውጣት ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው የሰበታ ከተማው ፋሲል ገ/ሚካኤል አንዱ ነው ። ከላይ ከተጠቀሱት ተጫዋቾች በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን ፣ የድሬደዋ ከተማው ወንደወሰን ደረጀ ፣ የወልቂጤው አብድልከሪም ወርቁ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ተጫዋቾች ናቸው ።
ከግብ ጠባቂዎች ጋር በተያያዘ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ግባቸውን ባለማስደፈር ፍሬው ጌታሁን ፤ ጀማል ጣሰው ፤ መሳይ አያኖ ብቸኞቹ ኢትዮጵያዊው ግብ ጠባቂ መሆን ሲችሉ ማሊያዊው ሚኬል ሳማኪ እና ቤኒያዊው ሀሪሰን ሄሱ በተመሳሳይ የመጀመሪያውን ደረጃ መያዝ የቻሉ ግብ ጠባቂዎች ናቸው ።
በቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ አሰልጣኞች ብቃታቸውን አሳይተው ሲያልፍ በዚህ ወር አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ፣ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እንዲሁም አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ የመጀመሪያዎቹ አሰልጣኞች ናቸው ። አምና ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘውን ሀድያን በመረከብ የሚያቋቸውን በርካታ ተጫዋቾች በመሰብሰብ የሊጉ መሪነት ላይ ያስቀመጡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ብቸኛው ሽንፈት ያልቀመሱት አሰልጣኝ ናቸው ።
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በተቋረጠው የውድድር ዓመት ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ኳስን መስርቶ በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ላይ መሰረትን አድርጎ በፀናው የጨዋታ ፍልስፍናቸው በዘንድሮው የውድድር ዓመት ላይ ከሌሎች ክለቦች በተሻለ በተጋጣሚ ላይ በርካታ ጎሎችን በማሳረፍ ቀዳሚው ክለብ ነው ። ቡናማዎች በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ግብ አስተናግደው ለመውጣት ተገደዋል ። አምና ወደ ሊጉ ካደጉ በኋላ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉት የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን ወልቂጤ ከተማም እስከ አራተኛው ሳምንት ድረስ ሽንፈት ያልቀመሰ ቡድን ሲሆን ወጣት ተጫዋቾችን ልምድ ካላቸው ጋር በማቀናጀት በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ይገኛሉ ።
በርካታ ሁነቶችን አሳይቶን ያለፈው የ ቤት ኪንግ ያለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ከመጪው አርብ ጀምሮ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ለሚቀጡሉት አንድ ወራት መካሄዳቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል ።