በይስሐቅ በላይ
የወትሮው ፈገግታው ከፊቱ እንደጉም
በኖ ጠፍቷል፤ከመጫወት ብዙ
ከመናገር ይልቅ መሬት መሬት እያየ
መተከዝንም ከመረጠ ቀናቶች ተቆጥሯል፤
ከ50 አመት በላይ ያስቆጠረ ጓደኝነት
ያለውና የወንድም ያህል የሚቆጥረውን
ታላቁን አሰልጣኝ ስዩም አባተ በጨካኙና
በክፉው ሞት በመነጠቁ በደረሰበት መራር
ሐዘን ውስጡ በሀዘን ተኮማትሯል፡
፡ ከአንድም ሁለቴ የሳምንቱ The Big
Interview አምድ እንግዳ ለማድረግ ያደረኩት
ሙከራ በፊቱ ገፅታ ላይ በሚነበበው የጠነከረ
የሀዘን ስሜትና ቁጭት ምክንያት በፍራቻ
ሳይሳካልኝ ቢቆይም አመጣጤ የሀዘን
ስሜቱን ለመጋራትና በሞት የተለየውን
የታላቁን አሰልጣኝ ስዩም አባተ ስም ከፍ
አድርገን ለማንሳት በመሆኑ ትንፋሼን
አሰባስቤ ቃላቶችን አምጬ “…አስራት
እንዴት ነህ… ስዩም አባተን… በማጣትህ…
ከደረሰብህ… መሪር ሐዘንስ በረታህ….?”
በማለት በሁለታችን መሀል የግድግዳ ያህል
ሆኖ የነበረውን የዝምታ ድባብ የሚያፈርስ
ጥያቄ ወረወርኩለት፡፡ እሱም ቀና ብሎ
ሳያየኝ መሬት ላይ የተተከሉትን አይኖቹን
በእጁ እያሻሸ በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ
በሐዘን በተሰበረ አንደበት…. “…የሞተ
ተጎዳ እንጂ… እኔ ምን እሆናለሁ…?”፤ …
ስዩም… መዳንን እንደተመኘና እንደተሰቃየ…
ማለፉ… ሐዘኔን የከበደ አድርጎታል…
እንግዲህ ምን ይደረጋል… እሱ ይሁን
ያለውን የፈቀደውን… መቀበል ብቻ ነው…”
የሚል ምላሽ ሰጥቶ ሳያበቃ ግድቡን ጥሶ
ለመፍሰስ እንደሚታገል ደራሽ ውሃ በድንገት
የአይኖቹን ግድቦች ጥሰው ለመፈሰስ
የተጣደፉት እንባዎቹን ለመጠራረግ እየሞከረ
ረዥም ሰዓት ዝም አለ፡፡
በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ አስራት ኃይሌን
ማናገር ከባድ መሆኑን በማወቄ የረዥም
ጊዜ ትዕግስትና ጥበቃ በማድረግ ጨዋታ
በመቀየር ከብዙ ማግባባት በኋላ በኢትዮጵያ
እግር ኳስ የ52 አመት አገልግሎት
ያለውን፣ ከአገሪቱ ክለቦች በላይ በግሉ
36 ዋንጫዎችን ያነሳውን፣ በአሁን
ሰዓት እሱ በተጨዋችነት ዘመናቸው
ያሰለጠናቸው ከ15 ያላነሱ ሙያተኞች
ዛሬ ፕሪሚየር ሊጉን ስለማጥለቅለቃቸው፣
ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ በኋላ
የፌዴሬሽኑን ስልጣንን ከተቆናጠጡት
ፕሬዚዳንቶች እጅ ሽልማትና እውቅናን
ስለማግኘቱ፣ በዋናነት ደግሞ በቅርቡ
በሞት ስለተነጠቀው የ55 አመት የልብ
ጓደኛው ስዩም አባተ ህልፈት የሀትሪክ
ጋዜጠኛ ማኔጅንግ ኤዲተር
ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ 52 የስኬት
አመታትን ያሳለፈውን ብቸኛውን
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን አነጋግሮት
ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፡፡
ሀትሪክ፡- ስዩምን በአንተ አንደበት ግለ
ፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምትገልፀው…. ?
- ማሰታውቂያ -
አስራት፡- (…. ረዥም ሰዓት… መሬት…
መሬት… እያየ… ዝም… አለ…)… ስዩም…
ለእኔ… የሙያ ጓደኛዬ ብቻ አይደለም…፤
…ስዩም… ወንድሜ…፣… ጓደኛዬ…፣ …
አብሮ አደጌ…፣… የሙያ… አጋሬ… ብቻ…
ሁሉም ነገሬ… ነው ብለው… ይቀለኛል፡፡
ከስዩም ጋር በትንሹ 54 እና 55 ዓመታት
አካባቢ አሳልፈናል፤ …መወለድ ቋንቋ ነው…
እንደሚባለው… ከአንድ እናት ማህፀን
ባንወለድም… ከሥጋ ወንድሞቼ በላይ…
የመንፈስ ወንድሜም ነው….፡፡ ….ከስዩም
ጋር… ለክለብም… ለብ/ቡድንም… አብረን
ተጫውተናል፣ በአንድ ሙያ አሳልፈናል፤
ሙሉ ህይወታችንን ለእግር ኳስ ሰጥተናል፤
ከእኔ ጋር ከአንድ እናት አባት የተወለደው
ወንድሜ ከስዩም ጋር ያሳለፍኩትን ያህል
አሳልፏል ማለት ይቸግረኛል፡፡ በአጠቃላይ
ስዩም አብሮ አደጌ፣ ጓደኛዬ፣ የሙያ አጋሬ፣
ወንድሜ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ደረጃ የገለፅከው
ስዩምን በሞት መነጠቅህን እንዴት አምነህ
ተቀበልከው… ?
አስራት፡- (አሁንም…ረዥም ሰዓት…
ዝምታ)… የሚገርምህ… ስዩም… ህይወቱ
ካለፈ ቀናቶች ተቆጥረዋል…፤…ዛሬም ግን…
ውስጤ… ይሄንን አምኖ… ለመቀበል በጣም
ተቸግሯል…፡፡ ከሆነ…ሰመመን…ከሚመስል
ነገር… ውስጥ… ስነቃ ነው… ስዩም…
አጠገቤ አለመኖሩን… በሞት መነጠቁን…
የ ማ ው ቀ ው … ፡ ፡ … ው ስ ጤ … ከ ወ ት ሮ ው
በተለየ…መልኩ… ስዩም… ስዩም… እያለ…
ይረብሸኛል…፤…ያለ… እየመሰለኝ… ሄጄ
ልጠይቀው…፣…ልደውልለት…ሁሉ…
አስብና…እንደገና…ደንግጬ…እተወዋለሁ፡
፡ …ያሳለፍነውን ነገር… ወደ ኋላ…
ተመልሼ… አስታውሼ… አይ የሰው ነገር
ብዬ… ምርር… ብዬ ብቻዬን… አለቅሳለሁ…፡
፡ …ያንን የመሰለ ጀግና… ያንን የመሰለ
ለሀገር ትልቅ ውለታን የዋለ አሰልጣኝ….
በዚህ ደረጃ… ተሰቃይቶ… ማለፉ…. ውስጤን
እርር ድብን… ያደርገዋል…፡፡ …በህመሙ
ጊዜ… ከጎኑ በመሆን አስታምሜዋለሁ…፤
…የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ ከሌሎች
የሙያ ጓኞቼ ጋር በመሆን የምንችለውን
ጥረት ብናደርግም ስዩምን እንደ ተመኘነው
ልናተርፈው አለመቻላችን ያንገበግበኛል፡
፡ በተለይ… በተለይ… የህመሙን የስቃዩን
መጠን ሳስበው እረበሻለሁ፤ ስቃዩ የበዛ
ነበር፤ ስቃዩን አልካፈለው ነገር የማይሆን
ነው፤ ብቻውን ተሰቃይቶ ማረፉ እየመጣብኝ
ይረብሸኛል፤ ግን ምን ታደርገዋለህ…፤ …
ሞት… ለሁላችንም የማይቀር… እንደሆነ
ባውቅም… ስዩም በዚህ ደረጃ… መሞቱ
ግን… ሐዘኑን… የከበደ አድርጎብኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …ስዩም… ታሞ አልጋ…
ላይ… በወደቀ ጊዜ… አንድ ነገር… ሲጠየቅ…
ከቤተሰቦቹ… ባልተናነሰ… “አስራትን
ጠይቁት”… ይል እንደነበር… ሰምቻለሁ…
፤ይህ ነገር… በመጨረሻው ሰዓትም… ለአንተ
ያለው ፍቅርና እምነት አለመውጣትን ጠቀነ
ነበር ማለት አይቻልም….?
አስራት፡- …እንደዚህ አይነት
ነገሮች ናቸው…ወደ አዕምሮዬ…እየመጡ
የሚረብሹኝና ሠላሜን የሚነጥቁኝ…፤…
ስዩም እንኳን… ታሞ አልጋ ላይ ወድቆ
ተወውና… ከመታመሙ በፊት ባሉት
አመታትም… ከእኔ ስር አይጠፋም ነበር…፡
፡ ደስታውንም፤ ቁጭቱንም፤ ብሶቱንም ለእኔ
ነበር የሚተነፍሰው…፡፡ አብረን ያደግን፣
አብረን የተጫወትን በመሆኑ… ስዩም
እኔን ያውቀኛል… እኔም እሱን ጠንቅቄ
አውቀዋለሁ…፡፡ ስዩም… ደስታም ይሁን…
ችግር ሲያጋጠመው… ሮጦ የሚያካፍለው
ለአኔ ነው…፤ …እኔም አንድ ነገር ሲኖር…
ሮጬ ለእሱ ነው የማወራው…፤…ለስዩም…
ምስጢረኛውም አማካሪውም… የሆንኩ ያህል
አድርጎ ነው የሚያስበኝ…፡፡ ታሞ አልጋ
ላይ ሆኖ እንኳን… አንድ ነገር ሲፈጠር…
አስራትን ጠይቁት… አስራትን ጥሩልኝ
ነው… የሚለው… (ረዥም… ዝምታ)… ግን
ምንታደርገዋለህ…?
ሀትሪክ፡- … ስዩም የመዳን .. ተሽሎት..
በሙያው የማገዝ ጉጉቱ ከፍተኛ ነበር የሚል
ነገር ሰምቻለሁ… ስለ እሱስ ምን ትላለህ… ?
አስራት፡- …ውይ…እሱን …አታንሳው…
ስዩም የመዳን…ተሽሎት…ወደ ቀድሞ ህይወቱ
የመመለስ ጉጉቱ በጣም ከፍተኛ ነበር…፤…
እንደዛ… ፈውስን እንደተመኘ… ለመዳን
እንደጓጓ ነው …ጉጉቱ ሳይሞላ… የተለየን…
ሀትሪክ፡- …የስዩም ሞት ይበልጥ
እንዲፈጥን… የአሰልጣኝነት ሙያው… ትልቅ
አስተዋፅኦ አድርጓል በማለት… ሙያውን…
ለሞቱ ዋነኛው ምክንያት… አድርገው
የሚናገሩ አሉ… ይሄንን… አባባል…
አንተስ… ትቀበለዋለህ…?
አስራት፡- …ምን ጥያቄ… አለው…? …
ስዩም… ህይወቱ በሞት እንዲነጠቅ… ሞቱ
እንዲፈጥን… የአሰልጣኝነት… ሙያው
ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል…፤…ስዩም… አሰል
ጣኝ… እያለ ድሮ የመጡበት ከሙያው ጋር
በተያያዘ በተፈጠረበት ጭንቀት
(ስትረስ) እና ከውጤት
ማጣት ጋ በተያያዘ በሚፈ
ጠርበት ብስጭት ውስጡ
በመጎዳቱ ነው፡፡ በእኛ
የ አ ሰ ል ጣ ኝ ነ ት
ዘመን እንደ አሁኑ በመቶ ሺዎች በሚሊዮን
ብሮች የሚከፈል ነገር ባይኖርም ህዝቡን
ለማስደሰት የሀገሪቱን ስፖርት ለማሳደግ
ከውስጣችን ተጨንቀን እንቅልፉ አጥተን ነው
የምንሰራው፡፡ ተሸንፈን ደጋፊው ተበሳጭቶ
ሲሄድ አንድ ቀን አይደለም ሁለት ሶስት ቀን
እንቅልፉ ባይናችን ሳይዞር ነው የምናድረው፡
፡ ይሄ ለከፋ ጭንቀትና ለብስጭት እየዳረገን
ጤናችን ተቃውሷል፡፡ ስዩምም የዚህ ችግር
ሰለባ ነበር፡፡ ከአንዴም ሁለቴ ልምምድ እየሠራ
ራሱን ስቶ ወድቋል፡፡ እኔም ተመሳሳይ ነገር
አጋጥሞኛል፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳን ጆሮዬን
ለከፋ ህመም ተዳርጌ ዶክተሩ “ከጭንቀት
(ስትረስ) የመጣ ነው በፍጥነት ከዚህ ሙያ
ካልወጣህ ለህይወትህ አደጋ አለው” ብሎ
አስጠንቅቆኝ ነው ከምወደው ስልጠና የራኩት፡
፡ ስዩም ልክ እንደ እኔው ሙያው እያለው
እውቀትና ውጤት፣ ልምድ እያለው መስራት
በሚቸልበት ጊዜ ከቦታው መገፍተሩ ህይወቱን
ሙሉ ሲያበሳጨው ለከፋ ችግር ሲዳርገው
ነው የኖረው፡፡ የአልጣኝነት ሙያ አሁን
ቀላል ነው፤ ተሸንፈህ ሁሉ ስቀህ ልትሄድ
ትችላለህ እኛ ግን ይሄ አልፈጠረብንም፡
፡ የህዝቡ መበሳጨት ያበሳጨናል፤ ውጤት
ማጣቱ እንቅልፍ ያሳጠናል፤ ታመን እንኳን
መች ጨክነን እንተኛለን፤ እየታመምን ነው
ስንሠራ የነበረው፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ደረጃ ዋጋ በከፈለለት
ሙያው ምን አትርፏል…?
አስራት፡- … ማን ስዩም…? ምን
አትርፏል…?ያልከው በገንዘብ በሀብት ደረጃ
ማለትህ ነው…? ይቅርታ.. አድርግልኝና…
ስዩም በሙያው ከበሽታ…፣ ከሞቱ ውጪ
ምንም ያተረፈው ነገር የለም…፤ ምናልባት
አተረፈ የምንለው ነገር ቢኖር ራሱን በሽታ
ላይ፣ ቤተሰቦቹን ችግር ላይ ጥሎ በርካታ
ተጨዋቾችን ለሀገር ማፍራቱን ነው፤ በዚህ
ካልተፅናናህ በስተቀር ሙያው ህይወቱን
ከመንጠቅ ውጪ በሙያው ያፈራው ሀብትም
ንብረትም የለም፡፡ ስዩም ታሞ በወደቀ ጊዜ
እንኳን ለህክምና ወጪ የሚሆነው ገንዘብ
ደጋግና ለባለውለተኞች ፈጥነው ደራሽ የሆኑ
ሰዎች ባደረጉለት ድጋፍ ነው፡፡ በእኛ ጊዜ እንደ
አሁኑ በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮን ብር
የሚከፈል ገንዝብ አልነበረም፤ በ400 አና 500
ብር በጣም ከፍ አለ ከተባለ በ5 ሺህ ብር
ደሞዝ ነው ስናሰለጥንና ያንን ሁሉ ውጤት
ስናመጣ የነበረው፡፡ ከዚህች ገንዘብ ቤተሰብ
አስተዳድረህ፣ ልጆች አስተምረህ እንዴት
ጥሪት ልታተርፍ ትችላለህ? አይታሰብም፤
ከሀብት ንብረት ይልቅ ስዩም በመቶ ሺህ
የሚጠጉ ተጫዋቾችን አፍርቷል፤ ሚሊዮኖችን
አስደስቷል፤ ለሀገር እግር ኳስ ትልቅ
አስተዋፅኦን አድርጓል፡፡ ከዚህ ውጪ ስዩም
ሀገርን ጠቅሞ ቤቱን ግን ባዶ አድርጎ ነው
ያረፈው፡፡ የስዩም ስም ከውጪ ስታየው ግዙፉ
ነው ወደ ቤቱ ስትገባ ግን በሙያው ያተረፈው
ምንም ነገር የለም ባዶ ነው ፡፡
ሀትሪክ፡- የስዩምን ህይወት ለመታደግ
የተደረገው ርብርቦሽ ለሀገር ከሰራውና
ከከፈለው ጋር ፍፁም የተራራቀ ነው በሚል
ቅሬታ የሚያቀርቡ አሉ፤ አንተ የአስተባባሪ
ኮሚቴው ሰብሳቢ እንደመሆንህ በህመሙ ጊዜ
ተገቢው ድጋፍ ተደርጓል ትላለህ… ?
አስራት፡- ለዚህ ጥያቄ ምላሽ
የምሰጥህ በመጀመሪያ ስዩም በታመመ ጊዜ
ደንግጠው ከጎኑ የሆኑትን፣ የአቅማቸውን
የወረወሩትን፣ በየቤታቸው ሆነው ምህረትን
በፀሎት የለመኑለትን ሁሉ በማመስገን ነው፡
፡ ስዩም ተሽሎት ጤንነቱ ተመልሶ ለማየት
ከመመኘት እጃቸውን በአቅማቸው የዘረጉትን
ግለሰቦችና ድርጅቶችን የኮሚቴው ሰብሳቢም
ስለነበርኩ ከልቤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ወደ እርዳታ አሰባሰቡ ስንሄድ የተገኘው ገንዘብ
ወደ 600 እና 700 ሺህ ብር አካባቢ ነው፤
የስጦታ ትንሽ ባይኖረውም አንድ ሚሊዮን
ብር እንኳን አልሞላም፡፡ ስዩም ለሀገር ከሰራው
ከባለውለተኛነቱ አንፃር ብሩ በቂ ነው ወይ?
ይሄንን ሰው ይፍረድ ከማለት ውጪ ሌላ
ምንም ማለት አልፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ
ያገዙንን ማመስገኑን ነው የምመርጠው፡፡
በዚሀ በኩል በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ
ስዩምን ጨምሮ የሁለት ሰው የአውሮፕላን
የደርሶ መልስ ትኬት በነፃ በመስጠት ባንኮክ
ሄዶ እንዲታከም ስለረዳን በኮሚቴውም
በቤተሰቡም ስም የኢትዮጵያ አየር መንገድን
አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ቢ.ጂ.አይ
ኢትዮጵያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርና
የደጋፊዎች የመረዳጃ ዕድር፤የኢትዮጵያ
ቡና ስፖርት ክለብና የደጋፊዎች ማህበር፣
የመቐለ ከተማ ስፖርት ክለብ፣ የሐዋሳ ከተማ
ስፖርት ክለብ፣ የኢትዮ መድን እግር ኳስ
ክለብ የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልናልና እነሱም
ለመልካሙ ስራቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ከዚህ ውጭ በእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ውስጥ
ተሳትፈው ጊዜያቸውን ሰውተው የተገኘው
ገንዘብ እንዲሰባሰብ ጥረት ያደረጉትን የኮሚቴ
አባላት እኔን ጨምሮ አቶ አስናቀ ደምሴ(አዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር ዋና ፀሐፊ)፣
አቶ አለም አሰፋ፣ አሰፋ ክፍሌ፣ ሰውነት
ቢሻው፣ ጋዜጠኛ ሰይድ ኪያር፣ መንግሥቱ
ታደሰ፣ ንጉሴ ገብሬ፣ ፍትሀነገስት፣ ኤፍሬም
(የፊደል ባርና ሬስቶራንት ባለቤት) ፣ዳንኤል
(ጎተራ) እና ወንድሙ ሠለሞን አባተ ሁሉም
የስዩምን ህይወት ለመታደግ ደክመዋልና በዚህ
አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በቀጣይ ምንም ገቢ የሌላቸውን
የስዩም ቤተሰቦች ለማገዝ ወይም ለማቋቋም
ምን የታሰበ ነገር አለ…?
አስራት፡-እስካሁን ሁላችንም በደረሰው
ሀዘን ደንግጠን ትኩረታችን እዛ ላይ በመሆኑ
እስከአሁን የታሰበ ወይም የታቀደ ነገር
ባይኖርም የቤተሰቡ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ
በመሆኑ ሁላችንም ልናግዛቸው ልንደግፋቸው
ይገባል፡፡ እኔ እንደውም መጀመሪያ ላይ የነበረኝ
ሃሣብ ከተሰበሰበው ገንዘብም ይሁን ወደፊት
ከሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ በሀገር ውሰጥ
ታክሞ ለህክምና የሚውለው ውሎ እንደው
በሚተርፈው ገንዝብ የእለት ገቢ የምታመጣ
ለቤተሰብ አንድ ነገር የምትሸፍን ታክሲም
ብትሆን ተገዝታ ቀዳዳ ትደፍናለች ብለን
አስበን ነበር፤ ግን ስዩም ውጪ ሄዶ መታከም
አለበት በመባሉ ገንዘቧ አለቀች፡፡ አሁንም
የቤተሰቡ ጉዳይ አሳሳቢ ነው፤ ሙያው ጥሪት
ጥለህበት የምታልፍበት ሙያ ባለመሆኑ ስዩም
ለቤተሰቦቹ ጥሎት የሄደው ነገር የለም፡፡ ሃሳቡ
የተቀደሰ ሃሣብ ነው እንግዲህ ከሀዘኑ በኋላ
ገፋቶ መሄድና ቤተሰቡን መታደግ የስዩምን
ውለታ ለመመለስ እንደመሞከር ያስቆጥራል፡፡
ሀትሪክ፡- ስዩም በህይወት ዘመኑ እያለ
ለሀገር ካበረከተው አንፃር ተገቢውን ክብርና
ቦታ ባለማግኘቱ በጣም ይበሳጭ ይከፋ
እንደነበር አውቃለሁ፤ስለዚህ ጉዳይ አንተ
የምታውቀውን እስቲ አውራኝ… ?
አስራት፡- ሁሌም ሲንገበገብባቸው ከነበሩ
ነገሮች አንዱ ይሄ ነው፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ
ምንም በሌለበት ከገንዘብ ይልቅ ለሀገራችን
ለሙያችን ለፍተን እግር ኳሱን በቅብብሎሽ
እዚህ አድርሰን መገፍተራችን ከእኔ በላይ
ስዩምን በጣም ያንገበግበው ያስቆጨው ነበር፡
፡ እኛ ከለፋነው ይልቅ እግር ኳሱን የማያውቁ
ምንም አይነት አስተዋፅኦ የሌላቸው ሰዎች
እንዳሻቸው ስፖርቱን ሲዘውሩት ሲያይ
በጣም ያመው ነበር፡፡ ለእኛ ይሄ ነው
የሚገባን?ለውለታችን ይሄ ነው ክፍያው? እያለ
በጣም ይበሳጭ ነበር፤ ሀገራችንን በረዥም
አመት ልምዳችን፣ እውቀታችን በሙያችን
እናግዝ እንርዳ ባልን ለምን እንገፈተራለን?
ለምን በር ይዘጋብናል? የሚል ትልቅ ቁጭት
በውስጡ እንደያዘ እንዳለፈ አውቃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ አንፃር ስዩም የልፋቱን
የድካሙን ያህል ተገቢውን ክብር ሣያገኝ ነው
ያለፈው ብሎ መደምደም ሥህተት ነው…?
አስራት፡- …የምን ስህተት…? …
ደግሞስ የምን ክብር.. አመጣህ…? …
እኛ መች ለሀገር የሠራን ባለውለተኛን
ማክበር እናውቅበታለን…? …እኛን እንኳን
ተወንና ከእኛ በፊትም የነበሩት ባለውለተኞች
ውለታቸው ተበልቶ ተጥለው፣ ተረስተው፣
ተዘንግተው ነው ያለፉት፤ ታሪክ ሆነው
የቀሩት። የስዩም እጣ ፈንታም ከእነሱ የተለየ
አይደለም፡፡ ስዩም ለሀገር የሰራውን ያሀል
የልፋቱን የድካሙን ያህል ክብር ተሰጥቶት
ነው ያለፈው ማለት ይቸግረኛል፡፡ አንተ ክብሩን
ትላለህ ስዩም እኮ የት እንዳለ ሳይወታስ በምን
ሁኔታ ላይ እንዳለ እንኳን ሳይታወቅ ነው
አምልጦን የሄደው፤ በታመመ ጊዜ እንኳን
ስዩምን የሚያክል ባለውለተኛን ውለታው
ተቆጥሮ ከጎኑ ሊኮን ሲገባ ተለምኖለት እኮ
የታከመው፤ በሌላው አለም እንደ ስዩም ለሀገር
ውለታ የዋሉ ሰዎች የጀግና አያያዝ ነው
የሚያዙት፡፡ በችግራቸው ወቅት መንግሥትም
ፌዴሬሽንም ሁሉም ፈጥኖ ነው ከጎናቸው
የሚቆመው፡፡ እኛ መች ለዚህ ክብር በቃን?
ከዚህ ይልቅ እንደ ሽንኮራ መጥጦ መጣልን
ነው የምናውቅበት፡፡
ሀትሪክ፡- ስዩም በኢትዮጵያ እግር ኳስ
ደማቅ አሻራውን ጥሎ ያለፈ ባለውለተኛ ነው፤
አሁን በሞት ተለይቶናል… በቀጣይ ምን
የሚታወስበት ነገር አለ… ?
አስራት፡- …ነገርኩህ እኮ…! …ከዚህ
በፊት ውለታ ውለው ያለፉ ሰዎች የሚታ
ወሱበት የቆመ ነገር ቢኖር አሁንም ተስፋ
ታደርጋለህ፤ የስዩምም ካለፈው የተለየ ነገር
ስለማይጠብቀው ልክ እንደሌሎቹ ስዩምም
ታሪክ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ግን አንድ ትልቅ
መፅናኛ ምንድነው? ለስዩም ለስሙ መጠሪያ
የሚሆን ነገር እግር ኳሱ ባያደርግለትም
ስዩም በሰራው ትልቅ ስራ በሰው ልብ ውስጥ
በገነባው ትልቅ ሀውልት ሁሌም ሲታወስ
ሲዘከር ይኖራል፡፡
ሀትሪክ፡- የስዩም ስርዓት ቀብር በክብር
ሲፈፅም በርካቶች ሳሪስ በሚገኘው የአቦ
ቤተክርስቲያን ተገኝተው አስከሬኑን በክብር
ሸኝተዋል…፤ ይሄንንስ እንዴት ታዘብከው…?
አስራት፡- …እውነት…ነው… ህዝቡ
በነቂስ ወጥቶ ስዩምን በክብር ሸኝቶታል፤…
ፈገግ…እንደማለት…እያለ… ያንን ሁሉ ሰው
በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝቶ አስክሬኑን
ሲሸኝ ሳይ በአዕምሮዬ በቅፅበት ምን እንደመጣታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡- … ምን… መጣ…?
አስራት፡–…ምን አለ… ስዩም… ለአንድ
ሰከንድ… እንኳን ቀና ብሎ…ይሄን ሁሉ…
ሰው… ቢያይና… ውስጡ የነበረው መከፋት…
ቀለል ቢልለት…?… የሚል… ሃሳብ በውስጤ
መጥቶ ነበር… ምክንያቱም… ስዩም…
ከመሞቱ በፊት… ተረስቻለሁ ፣ተጥያለሁ፣
አስታዋሽ የለኝም በሚል ነገር ስሜቱ ክፉኛ
ሲጎዳ ነው የኖረው፤ የሚገርምህ እኔንም
ራሴንም በስዩም ቦታ አድርጌ ለሁላችንም
የማይቀረው ሞት መጥቶ ባልፍ ለካ ውለታዬን
አስታውሰው እንባቸውን የሚያፈሱልኝ በክብር
የሚሸኙኝ ወገኖች አሉኝ ብዬም እንዳስብ
አድርጎኛል፡፡ በዚህ በኩል ብፅናና ብደሰትም፣
ሐዘኔን የሚያስረሣ ነገር ባይም ሌላም
የታዘብኩት ነገር አለ…
ሀትሪክ፡- … ምንድነው የታዘብከው… ?
አስራት፡- …ከላይ የጠቀስኩት…
በመልካምነት… የሚነሣው ነገር… እንዳለ
ሆኖ… ይሄ ሁሉ የሰው ጎርፍ የቀብር እለት
የታየው ርብርቦሽ ሰው በቁሙ በህይወቱ
እያለ ቢሆን ይበልጥ ደስ ይል ነበር፡፡ ሰው
ሳይወድቅ፣ህይወቱ ሳያልፍ ቆሞ በህይወት
እያለ ይሄ ቢደረግ የታመመው ህመሙ
ይታገስለታል፤ ተስፋ የቆረጠው ተስፋው
ይለመልማል፤ ለካስ አይዞህ የሚሉኝ በርካታ
ሰዎች ከጎኔ አሉ፤ ለካስ የሚያስብልኝ
የሚቆረቆርልኝ ወገን አለኝ፣ ውለታዬም
አልተበላም ብሎ እንዲያስብ እንዲፅናና
ስለሚያደርገው ሰው ከመሞቱ በፊት በህይወት
እያለ ቢለመድ መልካም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አስራት… እስቲ አሁን
ደግሞ …የሐዘን ድባብ… ከተላበሱ…
ጥያቄዎች ወጥተን… አንተን ትኩረት… ወደ
አደረጉ… ጥያቄዎች… ብናመራ… ምን …
ይመስልሃል?
አስራት፡- አይ.. አሁን… በዚህ ስሜት
ውስጥ… ሆኜ… አንተን የሚያረካ…
ለአንባቢዎችህ… የሚጠቅም ምላሽ…
ታገኛለህ… ብለህ ነው…?…እንግዲህ…
አንዴ… መጥተሃል.. ይሁን ካልክ…
እንቀጥል… ችግር… የለም…
ሀትሪክ፡- …ረዥሙን የህይወትህን
ክፍል… ለእግር ኳስ… ገብረህ ነው
ያለፍከው…፤ በእነዚህ አመታት ምን ያህል
ዋንጫዎችን እንዳገኘህ ታውቃለህ… ?
የቆጠርክበት አጋጣሚስ አለ?
አስራት፡- …እንደመሳቅ እያለ… ወደ 36
ዋንጫዎች አይሆኑም ብለህ… ነው…? አሁን
በቅርቡ የእኔንም ማስታወሻ ሣይ ሰዎችም ልክ
የራሣቸው ታሪክ ያህል አድርገው መዝግበው
ያመጡልኝን ሊስት ስመለከት በክለብናበብሔራዊ ቡድን በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት
ወደ 36 አካባቢ የሚሆኑ ዋንጫዎችን በግሌ
አግኝቻለሁ፡፡ ራሴን አግዝፌ ለማሳየት ፈልጌ
አይደለም እውነቴን ነው የምልህ የእግር ኳስ
ህይወቴ በሙሉ በድልና በሻምፒዮናነት የታጀበ
ነው፤ በየሄድኩበት ዋንጫ፣ በየሄድኩበት
ሻምፒዮን እየሆንኩ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄ ከክለቦችም በላይ ትልቅ
የስኬት ታሪክ ነው….፤ በኢትዮጵያ እግር
ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት ከተሾሙት
ፕሬዚዳንቶች ከሁሉም እጅ ሽልማት
በመቀበልም ብቸኛው ሰው ነህ ሲሉ ሰማሁ
እውነት ነው…?
አስራት፡- … አሁንም ሳቅ… የሚገርምህ
ነፍሳቸውን ይማርና ከጋሽ ይድነቃቸው በኋላ
በፕሬዚዳንትነት ወደ ፌዴሬሽኑ ከመጡት
ፕሬዚዳንቶች ሁሉ ሽልማትና እውቅና
አግኝቻለሁ፤ ከእነ አቶ ተስፋዬ ገብረየሱስ
ጀምሮ ባለፈው እስከ ወረዱት የፌዴሬሽኑ
ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህ እጅ በኮከብ
አሰልጣኝነትና በሻምፒዮንነት (በፎቶግራፍ
አስደግፎ እያስየኝ) ሽልማቶችና እውቅና
ተሰጥቶኛል፤አሁንም ስለተገፋሁ እንጂ ከአቶ
ኢሳያስ እጅም መቀበሌ አይቀርም ነበር …
ሳቅ…፤ ረዥሙ የእግር ኳስ ህይወቴ
ያተረፈልኝ ብዙዎች ያላገኙትን ትልቅ ትርፍ
በመሆኑ የተለየ የደስታ ስሜት ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ሀገሪቱን በአሰልጣኝነት
ያጥለቀለቁት አሰልጣኞች በሙሉ በተጨዋ
ችነታቸው ዘመን የአንተን የስልጠና በረከት
ቀምሰው ታላቅ አሰልጣኝ ለመሆን የበቁ ናቸው
በሚል የሌላ ታሪክ ባለቤት እንደሆንክም
በተለያየ መንገድ አረጋግጫለሁ… አንተ… ግን
ይሄንን… ታውቃለህ… ?
አስራት፡-… እንዴት ይሄን አስብከው
ባክህ…? (በመገረም ስሜት እያየኝ)….
እንደዚሁ አንዳንዶቹን የእኔ ልጆች ናቸው
ከማለት ውጪ በዚህ ደረጃ ብዛት እንዳላቸው
አላውቅም ነበር፤ አሁን ስታነሣው ግን አሁን
በፕሪሚየር ሊጉም በተለያዩ ክለቦች በማሰልጠን
ላይ የሚገኙት አሰልጣኞች በተጨዋችነት
ዘመናቸው እኔ አሰልጥኜያቸው ከእኔ ስልጠና
ትንሽም ብትሆን ትምህርት አግኝተው እዚህ
የደረሱ ናቸው ብዬ እንዳሰብ አድርጎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለአንባቢ ግልፅ ለማድረግ ያህል
ብንዘረዝራቸውና እነማን እንደሆኑ ቢታወቁ
ምን ይመስልሃል… ?…እኔ ባለኝ መረጃ ከ15
አይበልጡም…?
አስራት፡– ኡ… ሁሉንም…መዘርዘ
ቦታህን ማጣበብ አንባቢንም ማሰልቸት..
አይሆንም….?
ሀትሪክ፡- … ለማሳያ… የተወሰኑትን…
እናንሳ እስቲ…? አስራት፡- …አንግዲህ… ካነሣነው
አይቀር… በማስረጃ ላሳይህ… (በፎቶ እያሳየ)….
በተለይ በፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ካሉት
አሰልጣኞች ውስጥ…. እኔ አሰልጥኜያቸው
አሰልጣኝ የሆኑት… ገ/መድህን ኃይሌ፣
ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ዮሐንስ ሳህሌ፣ውበቱ
አባተ፣ጳውሎስ ጌታቸው(ማንጎ)፣ ፋሲል
ተካልኝ፣ ዘሪሁን ሸንገታ፣ ሙሉጌታ ምህረት፣
ውብሸት ደሳለኝ፣ ፀጋዘአብ አስገዶም፣ ዕድሉ
ደረጀ፣ መሐመድ ኢብርሂም (ኪንግ)፣ሳምሶን
አየለ፣ ደግአረገ እነዚህ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ
ናቸው፡፡ ዛሬ ፕሪሚየሪ ሊጉን ያጥለቀለቁት
አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመናቸው የእኔን
ስልጠና በደንብ አጣጥመው፣ አሰልጣኝነት
ማለት ምን ማለት? እንደሆነ በእኔ ውስጥ
አይተው ወደ ስልጠና የመጡ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ያሰለጠንካቸው ተጨዋቾች
ዛሬ አሠልጣኝ ሆነው በዚህ ደረጃ ፕሪሚየር
ሊጉን ወረውት ስታይ ምን ይሰማሃል…?
አስራት፡- በጣም ነው የምደሰተው፤ ዛሬ
አሰልጣኝ ከመሆናቸው በፊት በቀጥታም
ይሁን በተዘዋዋሪ በእኔ ሥር ሲሰለጥኑ በቂ
ትምህርት እንደወሰዱና ለዛሬው ማንነታቸው
ተፅዕኖ እንዳሳረፍኩባቸውም ይሰማኛል፡፡ ከላይ
የዘረዘርኩልህን በክለብ ብቻ ሣይሆን በብ/
ቡድን ደረጃም አሰልጥኜያቸዋለሁ፡፡ በእኔ
ስር ስልጠነው ለዚህ ክብር በመብቃታቸው
ደስተኛ ነኝ፤ አሰልጣኝነት ማለት… ማሰልጠን
ማለት… ምን ማለት…? እንደሆነ…
ወደ ሙያው ከመምጣታቸው በፊት በእኔ
ተምረዋል…፡፡ ልፋቱን፣ ድካሙን አይተው…
ነው ወደ ሙያው የመጡት…፤ በረዥሙ
አመት የስልጠና ህይወታችን ከውጤት በዘለለ
ለእግር ኳሱ ያበረከትነው ትልቁ ትርፍም
ይሄ ነው፤ በዚህም በጣም እፅናናለሁ፤
እደሰታለሁም፡፡
ሀትሪክ፡- በርካታ ተጨዋቾችን
“አይመጥኑም” ወይም ብቃታቸው “ደካማ ነው”
ተብለው ሲቀነሱ የተጨዋችን ብቃት ለይቶ
በሚያውቀው የተለየው አይንህ የብዙዎችን
የእግር ኳስ ህይወት በመታደግ ከራሳቸው
አልፈው ሀገርን የሚጠቅሙ ተጨዋቾች
በማድረግም ትታወቃለህ፣ ለማሳያ ያህል ዛሬ
በፕሮፌሽናልነት ግብፅ የሚጫወተው ዑመድ
ኡኩሪ በዋናነት ይጠቀሳል… እስቲ ይህንን
አጋጣሚ ወደ ኋላ ተመልሰህ አጫውተኝ…?
አስራት፡- አንተ ዑመድን ለይተህ አነሳህ
እንጂ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ብዙ
ናቸው፤ የዑመድ ኡኩሪ ምን መሠለህ…? …
ዑመድ ለታዳጊ ብ/ቡድን ከጋምቤላ ታጭቶ
ይመጣና አቃቂ ላይ ምርጫ ይደረጋል…
በወቅቱ እኔ የመከላከያ አሰልጣኝ ነበርኩ…
ተጨዋች ለመመልመል በቦታው ተገኝቼ
ምርጫውን ስከታተል ዑመድን “ብቁ
አይደለም.፤ አይመጥንም” ብለው ይቀንሱታል፡
፡ ዑመድ ገና ትንሽ ነው ግን የኳስ አያያዙን
ሳየው በውስጡ የሚያድግ ትልቅ ነገር
አለው፤እነሱ ቀንሰውት በጣም አዝኖ ሲወጣ
እሱንና በረከት የሚባልን ሌላ ታዳጊ ተጨዋች
ጠራኋቸውና እናንተ ከእኔ ጋር ትሰራላችሁ…
ስላቸው… ሁለቱም አላመኑም… “እ…ጋሼ…
ምን አልክ…? እኔ…ጋ… ትሰራላችሁ ነው
ያልከው….?” ብለው የተናገርኩትን ደግመው
ጠየቁኝ አዎን እኔ ጋ ትሰራላችሁ አልኳቸውና
እንደውም ዛሬ የትም አትሄዱም ምሣም ከእኔ
ጋር ነው የምትበሉት ስላቸው የሚሆነውን
ሁሉ ባለማመን ደነገጡ፡፡
ሀትሪክ፡- … ከዚያስ…. ?
አስራት፡-… ከዚያ ምሣ ሌላ ቦታ ሣይሆን
እቤቴ ነው የምጋብዛችሁ ብዬ ወደ ቤቴ
አመጣኋቸውና ምሣ አብረን እየበላን እናንተ
እኔ የምላችሁን ከሰማችሁ፣ የማሰራችሁን
ከሠራችሁ ትልቅ ቦታ ትደርሳላችሁ በተለይ
ዑመድ ጥሩ ነገር አለህ ትልቅ ደረጃ
አደርስሃለሁ ብያቸው ነገ ሜዳ ትመጣላችሁ
ብዬ ሸኘኋቸው፤ ባልኳቸው መሠረት በነጋታው
ትሬኒንግ ሜዳ መጡ፤ ከዚያ ተጨዋቾቹን
በሙሉ ሰብስቤ ወደ ዑመድ እያሳየሁ ይሄንን
ልጅ አያችሁት ነገ ትልቅ ተጨዋች የሚሆን
ነው ስላቸው አብዛኛው ተጨዋች በመገረም
ነበር የተመለከትኝ፤ ያው እንግዲህ መከላከያ
የወታደር ቤት በመሆኑ እነ ዑመድን ልምምድ
ከማስጀመሬ በፊት ማሳወቅ ነበረብኝ፤ ኮሌኔል
ምትኩ የሚባል የቡድን መሪ ነበሩ ለእሱ
ነገርኩት፤ እሱም “ትሬይኒንግ መስራቱን
ይሰሩ ምግባቸውስ?” አለኝ፡፡ እኔም ልጆች
ናቸው የምግቡ ችግር የለውም የእኔን ምግብ
ይመገባሉ አልኩት፡፡ ከዛ ልምምድ እንዲሰሩ
ለማስፈቀድ አሁን በህይወት የሉም የክለቡ
ኃላፊ ጄኔራል ኃይሌ የሚባሉ ነበሩ እሳቸው
ጋር ይዤያቸው ሄድኩና ጄኔራል እነዚህ ልጆች
ነገ ከክለቡ አልፈው ሀገርን የሚጠቅሙ ስሟን
የሚያስጠሩ ተጨዋቾች ይሆናሉ ትሬይኒንግ
እንዲሰሩ ይፈቀድልኝ ብዬ በክለቡ ህግ መሠረት
ጠየኳቸው እሣቸውም “አስራት ለሀገርም
ለክለብም ይጠቅማሉ ካልክና ካመንክባቸው
ይስሩ ግን ላብ መተኪያቸው ምግባቸውስ?”
ብለው እሳቸውም ጠየቁኝ እኔም ልጆች ስለሆኑ
ችግር የለም የእኔን ምግብ ይመገባሉ ስላቸው
“እሺ እንዳልክ” ብለውኝ ገና እግሬ ወጣ እንዳለ
አስጠሩኝና “አስራት በዚህ ደረጃ ካመንክባቸው
ለክለቡም ለሀገርም ይጠቅማሉ ካልክ
የአንተን ምግብ አይበሉም የራሣቸውን ምግብ
ፈቀጄላቸዋለሁ አሉኝ፡፡ በዚህ መሠረት ዑመድ
መከላከያ ተይዞ ልምምድን ጀመረ፡፡ በጣም
ጥሩ እየሆነ፣ እየተወደደ መጣ፡፡ ቀጠልኩና
ጄኔራሉን ቤተሰባቸውን እንዲረዱ ትንሽ ክፍያ
እንፈፅመላቸው ብዬ አሳመንኳቸው ጄኔራል
ቀናና ለስፖርት ጥሩ ስሜት ያላቸው ሰው
ስለነበሩ በወቅቱ ትልቁክፍያ ገንዘብ 10 ሺህ
ብር ነበር እነሱ ግን ልጆች ስለሆኑ በሚል
አምስት አምስት ሺህ ብር ተፈቀደላቸው፤
ለዑመድ አምስት ሺህ ብር ሲሰጠው “እንዴ
ጋሺ ይሄን ሁሉ ብር ምን ላደርገው ነው?”
ሲል በመገረም ጠየቀኝ አትገረም ገና ከዚህ
በላይ ታገኛለህ በርታ ይሄ ሞራል መጠበቂያ
ነው፤ ለቤተሰቦቻችሁ ላኩ አልኩት፤ በጣም
ተደሰተ፡፡ ከዚያ በኋላ በየወሩ ማግኘት ጀመረ፡
፡ እንደዚህ አያለ መከላከያ ውስጥ ጎልቶ
መታየት ጀመረ፡፡ ብቃቱን አይተው ጊዮርጊሶች
ወዲያው ወሰዱት፤ እንደዚህ እንደዚህ እያለ
የቀጠለው የዑመድ የእግር ኳስ ህይወት ዛሬ
ፕሮፌሽናል ሆኖ በግብፅ ሊግ እስከመጫወት
ደርሷል፡፡ ያኔ ዑመድን በገለፅኩት መንገድ
ባልመልሰው አሁን የሚገኝበት ደረጃ ይደርስ
ነበር? አላውቅም፤ ዑመድን ብቻ ሳይሆን ልክ
እንደእሱ ከመስመር ሊወጡ ያሉ ልጆችን
መልሼ ሀገርንም ራሣቸዉንም እንዲጠቅሙ
አድርጌያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የዑመድን አነሳን እንጂ
ሙሉአለም፣ ሳላሀዲን ባርጌቾ፣ አይናለም፤
አስራት መገርሣ ብርሃኑ (ፈየራ) አያስፈልጉም
ተብለው አንተ “ሞቼ እገኛለሁ፤ኃላፊነቱን እኔ
እወስዳለሁ” ብለህ ነው ዛሬ ለሚገኙበት ደረጃ
የበቁት የሚል ነገርም ሰምቻለሁ…. ?
አስራት፡- …ምንም ጥያቄ የለውም…
አሁን የዘረዘርካቸው ተጨዋቾችም በሙሉ
በተለያየ ምክንያት ሊቀነሱ ሲሉ እኔ ነኝ በፍፁም
መነካት የለባቸውም ብዬ የመለስኳቸው፡፡
ሙሉአለም ረጋሳ ከሲ ቡድን ሳሳድገው ብዙ
ተቋውሞዎች ነበሩብኝ፡፡ ሙሉአለም በወቅቱ
በጣም ትንሽና ቀጫጫ ስለነበረ…”ይሄንን
ነፍስ የሌለው ልጅ ለጊዮርጊስ?” በማለት
ከመቃወምአልፈው ዘመዴ ሁሉ የመሰላቸው
ሁሉ ነበሩ፡፡ እሱ ስኬታማ ባይሆን ኖሮ
ለእኔም ጦስ ሆኖ ከቡድኑ የምሰናበትበት
ሁኔታ ሁሉ ይፈጠር ነበር፤ እኔ ግን በወቅቱ
ኃላፊነቱን ለእኔ ተውት ዛሬ ነፍስ የሌለው
ተጨዋች ቢመስልም ነገ ጊዮርጊስን ተሸክሞ
የሚወጣ ልጅ እንደሆነ ታዩታላችሁ
አልኳቸው፤ ሣይኮሎጂስት ሆንክ እንዴ?
አትበለኝ እንጂ ከሙሉአለም ችሎታ ይልቅ
መጀመሪያ አይቼ የወደድኩት ፊቱን ነው፡፡
ፊቱን ስታየው በጣም ብልጥ ፊት ነው፤ በዚያ
ላይ ኳስ ይችላል፤ በብዙ ተቃውሞ መሀል
ያዝኩት፤ የመሰለፉ እድልም ሰጠሁት። ያው
ሁሉም እንደሚያውቀው ቦታውን የርስት
ያህል ለዓመታት ይዞት ሁሉንም አስፈንድቆ
የተቃወሙትን ሁሉ አንገት አስደፋ፡፡ ዛሬም
ስለ አማካይ ተጨዋች ሲነሳ ምን እንደሚባል
የምናውቀው ነው፡፡ ሳላሀዲንና አስራት
መገርሣንም መብራት እያለሁ የያዝኳቸው
ሁለቱንም የመረጥኳቸው እኔ ነኝ፡፡ በተለይ
አስራት መገርሣን ከሚቀነሱት ተጨዋቾች
ዝርዝር ውስጥ አድርገውት ደብረዘይት ምርጫ
ስናደርግ ሰጡኝ፡፡ከዚያ ሳየው ኳሱም ቁመቱም
ጥሩ ነው፤ አማካይ ቦታ እንኳን ቢጫወት
ቢቆምም ማንም እያልፈውም አልኩና
ከተቀናሽ ሊስት አውጥቼ ለዋናው ቡድን
ስመረጠው ኮሜቴዎቹ ተንጫጩብኝ፡፡ “ጋሼ
ከተቀናሽ አውጥተህ ለዋናው ቡድን?” ብለው
ተቃውሙኝ፡፡ በእኔ ይሆንባችሁ ይሄ ልጅ
ክለቡንም ሀገርንም ይጠቅማል አልኳቸው፡
፡ በዚህ ሁኔታ ተያዘ እንዳልኩትም ከክለብም
አልፎ የሀገሪቱ ምርጥ ተጨዋችና ብ/
ቡድኑንም ለመጥቀም በቃ፡፡
ሀትሪክ፡…ሳላሀዲን ባርጌቾስ… ?
አስራት፡- …ሳላሀዲንን መብራት እያለሁ
የቢ ቡድን ጨዋታ ስከታተል አየሁት፤ ቁመቱ
ጥሩ ነው፣ ደፋር ነው፣ ትልቅ ልብ ያለው
ተጨዋች ነው፣ ኳስም ይችላል፤ ከዚያ አበበ
ለሚባለው የቢ ቡድን አሠልጣኝ በአንድ ቀን
እይታ ብቻ ይሄ ልጅ እኔ ጋር ዋናው ቡድን
መጥቶ ይሰራ አልኩት፤ መጣ ዋናው ቡድን
ተይዞ መስራት ጀመረ፡፡ እኔ መብራትን ለቅቄ
ስወጣ ሳላሀዲን ባርጌቾም ዘመዴ መስሏቸው
ነው መሰለኝ አባረሩት፤ መድን እያለሁ አንድ
ቀን ቢሮዬ መጣ አለህ እንዴ ስለው “ምን ጋሼ
አንተ ከመብራት ስትወጣ እኔንም አባረሩኝ
እኮ” ሲለኝ እንዴ አንተን? በል አንተማ
ታስፈልገኛለህ ነገ መጥተህ ልምምድህን ጀምር
አልኩት፡፡ መድንን ተቀላቀለ፤ መድን ላይ
በሚያደርገው እንቅስቃሴ ጊዮርጊሶች ወደዱት፤
ወዲያው ጠለፉት፡፡ እሱም ዛሬ ከክለቡ
አልፎ የብ/ቡድኑ ምሶሶም ለመሆን በቅቷል፡
፡ ከእሱ ውጪም ብርሃኑ ፈየራ፣ አንተነህ
አላምረው፣ አይናለም ለምን ያዝካቸው የሚል
ተቋውሞ እየቀረበብኝ ተቋቋሜ የእግር ኳስ
ትስስራቸው እንዳይበጠስ ክለብንም ሀገርንም
እንዲጠቅሙ አድርጌያለሁ፡፡ የሁሉም
የየራሱ ታሪክ ያለው ሲሆን ስለአይናለም
አመጣጥ ደግሞ ልንገርህ፤አይናለም ወታደር
ነው፤ የጦሩ የውስጥ ውድድር በየአመቱ ይክሄዳል፤ ከዚያ ለኮሚቴውና ለአሰልጣኞች
ከውስጥ ውድድሩ የተሻለ ነገር ያላቸውን
መርጣችሁ ላኩልኝ አልኳቸው፤ ብዛት
ያላቸውን ወታደር ተጨዋቾች ላኩልኝ ከእነሱ
ውስጥ አይናለምን ጨምሮ ሶስት ተጨዋቾችን
መረጥኩ፡፡ አይናለምን ያየሁት ቀን ቁመቱም
ፍላጎቱም ችሎታውም ጥሩ ነው፡፡ ከተለፋበት
የሚለወጥ ልጅ ነው ብዬ ከወታደሮች መሀል
መርጬ ያዝኩት፡፡ እሱም እንዳያችሁት ከክለብ
አልፎ የሀገር መከታ እስከመሆን በቅቷል፡፡
የፀጋዘአብ አስገዶምም የራሱ ታሪክ አለው፤
እነዚህን ያስታወስኳቸው ጥቂቶቹን እንጂ ብዙ
ተጨዋቾች አሉ፤ ከመስመር ሊወጡ ሲሉ
የመለስኳቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት
በእግር ኳሱ ከ52 ዓመት የበለጠ አገልግሎት
አለህ፤ የልምድ፣ የእውቀትና የውጤት
ባለቤት ሆነህ ሀገሪቱ ግን በአንተ ከመጠቀም
ይልቅ በተለያየ ምክንያት ስትገፈትርህ
ነው የሚታየው… ይሄ ምን ስሜት
ይፈጥርብሃል…?
አስራት፡- … ይሄ… ነው ትልቁ ጥያቄ…!
እንዳልከው በእግር ኳስ ረዥሙን እድሜዬን
ከውጤት፣ ከስኬትና ከልምድ ጋር አጣምሬ
የያዝኩ ሰው ነኝ፡፡ በሌላ ሀገር ብኖር ፈልጌ
ሳይሆን ተፈልጌ ነበር የምሰራው፤ በሀገሬ ግን
የለፋሁለትን፣ የደማሁለትን እግር ኳስ ባለኝ
የተካበተ ልምድም እውቀት እባካችሁ ላግዝ
ልርዳ ብል የሚሰማኝ አላገኘሁም፤ ይሄ በጣም
ነው የሚያሳዝነኝ፤ የስዩምም አንደኛው ቅሬታና
ብስጭት ይሄ ነው፡፡ ስማችን ከውጤታማነትና
ከታሪክ ጋር ይነሣል በሌላ በኩል ከአካባቢው
እንገፈተራለን፤ በርም ይዘጋብናል፡፡ በሠራነው
ሥራ በሀገር ውስጥ ብቻ ሣይሆን በውጭም
ክብር አለን፡፡ ለማሳያ ያህል የካፍ ኤ
ላይሰንስ (ኢኩዊቫለንት ኮርስ) ሲሰጥ ሚ/ር
ሸኸታ የሚባል የካፍ ኢንስትራክተር አዲስ
አበባ መጥቶ ለእኛ ስልጠና ሲሰጥ “ይሄንን
የኢኩዊቫለንት ኮርስ በካፍ ደረጃ የምንሰጠው
ተጫውተው ላለፉ ላሰለጠኑ በእግር ኳሱ ትልቅ
ስራን ለሰሩ ሰዎች እውቅና የምንሰጥበት ነው፡
፡ እኛ እነዚህን ሰዎች ማሰልጠን አንችልም
እነሱ ብዙ ነገር አልፈው የሄዱ ሰስለሆነ ይሄ
ስልጠና ለእነሱ እውቅና የምንሰጥበት ነው”
ብሎ ከተናገረ በኋላ ምን እንዳለ ታውቃለህ…..
ሀትሪክ፡- ምን… አለ…..?
አስራት፡- … እኔን ጠራኝና፡፡ “ይሄን
ሰውዬ ታውቁታላችሁ? ታከብሩታላችሁ?
የዚህ ሀገር ትልቅ ሰው ነው፤ ብዙ ታሪክ ያለው
ሰው ነው እንደእነዚህ አይነት ሰዎችን አክብሩ”
ብሎ ምስክርነቱን ሁሉም አሰልጣኝ በተገኘበት
ሰጥቷል፡፡ ከሀገርህ ብዙ ርቀት ያለ ሰው
ስራህን ልምምድን አይቶ እንዲህ ያከብርሃል፤
በሀገር ቤት ደግሞ በር ይከረቸምብሃል፤ እነ
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዛሬም ከህመማቸው
ጋር እየተሰቃዩ ክለባቸውን እዲያግዙ ተደረገ
እንጂ በር አልተከዘጋባቸውም፡፡ የረዥም
አመት ልምድ፣ የውጤታማነት ታሪክ
እውቀት ያለው ሰው እንኳን ለምኖ ልሥራ
ብሎ ተወውና በባትሪ ተፈልጎ በማምጣት ነበር
ልንጠቀምበት የሚገባው፡፡ በእኛ ሀገር ያለው
በተቃራኒው ነው፤ የእለት የእለቱን ብቻ ነው
የምናሳስበው፡፡ ይሄ አካሄድ እኛን ብቻ ሳይሆን
ሀገር እንዳትጠቀምም መፍረድ ነው ለእኔ፡፡
ሀትሪክ፡- አስራት አካል ብቃት (ፊትነስ)
ላይ ማተኮሩ አሁን ላለበት ደረጃ አብቅቶታል
ማለት እንችላለን…?
አስራት፡- እንኳን ይሄን ነገር አነሳኸው፤
ሰዎች በግንዛቤ ችግር ወይም ነገሮችን ሆን
ብለው ሲደበላልቁ ታያለህ፡፡ እኔ እውነት
ነው ፊትነስ በጣም እወዳለሁ፤የፊትነስ
ስልጠናን ስሰጥ ግን ኳስን መሠረት አድርጌ
ነው። እናንተ ሚዲያዎችና አንዳንዶች
እያደበላለቁት ህዝቡን እያምታቱት እንጂ
ፊትነስን ከኳስ ውጪ ማሰብ አይቻልም፡፡
ማንኛውም አሰልጣኝ የፊትነስ ስራን ሲሰራ
ኳስን መሠረት አድርጎ ነው፤ ኳስን ሙሉ
ሜዳ አካሎ ለመጫወት የአካል ብቃታቸውን
(ፊትነሳቸውን) ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ እኔ
ፊትነሱን እወዳለሁ ስልህ የጉልበት ሥራን
ብቻ አሰርቼ ኳስን ሳላስነካቸው በኳስ
ሳላሰራቸው ሂዱ አልላቸውም፡፡ ምክንያቱም
ሰርተው ሠርተው እኮ ነገ የሚጫወቱት ኳስ
ነውና፡፡ ይሄን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች
ሲነገሩ አደምጣለሁ፤ “እከሌ የሚባል አሰልጣኝ
ኳስን መሠረት አድርጎ ነው የሚሠራው”
ሲባል እሰማለሁ፤ እነጋገሩ የተለየ ተአምር
እንደተፈጠረ ተደርጎ ነው፤ እውነታው ግን
ኳስን መሠረት አድርጎ የማይሰራ አሰልጣኝ
የለም፡፡ ዛሬማ ደፋሮች የበዙበት ጊዜ አይደለም?
የቡድን መሪዎች ሣይቀሩ “እኛ የቀጠርነው
አሰልጣኝ ኳስን መሠረት አድርጎ የሚሰራ
ነው” ብለው በድፍረት ሲናገሩ እየሰማን ነው፤
ይሄንን የቡድን መሪ ኳስን መሠረት አድርጎ
መስራት ምን ማለት ነው? ብትለው ማስረዳት
አይችልም፤ ግን ሲባል ሰምቶ እንዲህ ይላል።
ያለ ፊትነስ የትም መድረስ አይቻልም፡፡
ፊትነስ ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩት ምን
ውጤት እያመጡ እንደሆነ ያልሰሩት ምን
እየገጠማቸው እንደሆነ እያየን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፊትነስ (አካል ብቃት) ላይ
ትኩረት ማድረግህ ጎድቶሃል ወይ? አሁን
ለምትገኝበት ደረጃ አብቅቶሃል ወይ የሚለው
አልመለስክልኝም….?
አስራት፡- በፍፁም አልጎዳኝም…! አሁን
ለምገኝበት ደረጀ ያበቃኝ ወደ ክለብ የምትገባበት
መንገዱ የተለየ ሲስተም ስላለው ይመስለኛል፤
እኔ ሙሉ እድሜዬን በውጤታማነትና
በአሸናፊነት ያሳለፈኩ ሰው ነኝ፡፡ በትክክለኛው
መንገድ መመዘኛው ውጤትና እውቀት ብቻ
ቢሆንና ሌላ ሲስተም ባይኖረው ከስልጠና
ውጪ አልሆንም ነበር፡፡ ምክያቱም ከእኔ
ያነሰ የውጤት ታሪክ ያላቸው፣ ክለብ ለድል
ያበቁ ሣይሆን ያወረዱ አሰልጣኞች ከክለብ
ክለብ ያውም በከፍተኛ የፊርማ ክፍያ ደሞዝ
እየተገላበጡ ሲገቡ እኔ የክለብ ያለህ አልልም
ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በእግር ኳሱ ውስጥ ሰጥቶ
የመቀበል ነገር ያለ ይምስለኛል፤ እኔ ደግሞ
በዚህ መስመር ውስጥ አልሄድም፡፡ ለቀጣሪ
ክለቦችም አልመቻቸውም፤ከዚህ ከክለብ ቅጥር
ጋር በተያያዘ ስትጠይቀኝ አሁን በቅርቡ የሆነ
አንድ ነገር ትዝ አለኝ….
ሀትሪክ፡- … ምን ትዝ… አለህ… ?
አስራት፡-….. አንድ ሄዋን የምትባል
እንደ ኤጀንትነት ሆና የምትሰራ ልጅ “ጋሼ
አንተ ልምድና ውጤት ያለህ ትልቅ አሰልጣኝ
ነህ መቀመጥ የለብህም፤ ክለብ ባገኝልህ
ትሰራለህ ወይ…?” አለችኝ፤ እኔም አዎን ምን
ገዶኝ አልኳት። የእኔን እሽታ ካገኘች በኋላ
ስማቸውን የማልጠቅስልህ ሁለት ክለቦችን
ሄዳ አናገረች እነሱም “እንዴ ጋሽ አስራትን?
በደስታ” ካሏት በኋላ “እሺ መልስ እንሰጥሻለን”
ይሏታል፡፡ በኋላ ላይ ግን ትንሽ ቆይተው
“አይ… ይቅርታ… ሌሎች አሰልጣኞች
ተቀጥረዋል” ብለዋት ሁለት ቦታ ፌል
አድርጎባታል፡፡ በኋላ የተቀጠሩት አሰልጣኞች
የልምድና የውጤታማነት ታሪክ ከእኔ ጋር
የማይገናኝ ነው፤ በእርግጥ እኛ ያየንበት
መንገድ አለ ሊሉ ይችላሉ መብታቸው ነው፤
የእኔ ባህሪና ማንነት ስለሚታወቅ እነዚህ
ሰዎች ያሰቡትን ነገር ለማሳካት ስለሚቸገሩ
የሚመቻቸውን ሰው ወደ ቦታው አምጥተዋል፡
፡ ክለብ የምትገባበት መንገድ አሁን
ተቀይሯል፤መስፈርታቸውም ግራ ያጋባሀል፡፡
ቡድን ያወረደን ደካማ ውጤት በማስመዝገብና
ደካማ ቡድን በመገንባት የሚታወቅ አሰልጣኝን
ያውም ብር ጨምረህ የምትቀጥር ከሆነ ምን
እየተሠራ እንደሆነ ለማወቅ ጠቢብነትን
አይጠይቅም፡፡ ከዚህ በፊትም ብያለሁ በዚህ
የተበላሸ መንግድ ሄጄ እንጀራ ከምበላ አሁንም
መራቤን እመርጣለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ አይነት ታድያ ሙያህን
ልምድህን እቤትህ ይዘህ ልትቀመጥ ነው….?
በቀጣይስ ምን ለመስራት አስበሃል?
አስራት፡- በክለብ ሥራ ላይ ባልገኝም
አሁንም አልተቀመጥኩም፤ ከስልጠናም
ወጥቻለሁ ማለት አልችልም፡፡ ሙያውን
ከወደድከው ካፈቀርከው በህይወት እስካለሁ
ድረስ ከሙያው መራቅን አይቻለኝም፡፡ ዛሬ
ሥልጠና ሜዳ ላይ በመገኘት ብቻ አይደለም
የምትማረውው፤ምስጋና ለቴክኖሎጂ ቤትህ
ተቀምጠህ ትሰለጥናለህ ያለ አስተማሪ
ትማራለህ፤ በዚህም አስተሳሰብህ፣ እይታህ፣
እውቀትህ እየሠፋ ይሄዳል፡፡ ቡድን መያዝን
በተመለከተ ቡድን ለመያዝ በዋና አሰል
ጣኝነትም ባይሆን በአማካሪነት፣ በቴክኒክ
ኃላፊነት ለመስራት አስቤ ባልኩህ መንገድ
ፌል ቢያደርግም፣ የተዘጋው በር ባይከፈትም
ሙያዬን ስለምወደው ልምዴንና እውቀቴን
በለጋ ህፃናት ታዳጊዎች ላይ በማፍሰስ
ለመስራት እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ….. ማለት… አካዳሚ ልት
ከፍት….?
አስራት፡- አካዳሚ… አይደለም…!
በነገራችን ላይ አካዳሚ የራሱ ትርጉምና አካሄድ
አለው፡፡ የእኔ አካዳሚ አይደለም የታዳጋዎች
የማሰልጠኛ ማዕከል ነው፡፡ ታዳጊዎችን
በማሰልጠን ለሀገር ለክለቦች የሚጠቅሙ
ልጆች ላይ የረዥም አመት ልምዴን በማፍሰስ
ልጆችን እንደ እርሳስ የመቅረፅ ሃሣቡ አለኝ፡
፡ ለዚያም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረኩ ለሀገር
የሚጠቅም ሥራ ለመስራት እየተንደረደርኩ
ነው፡፡ በዚህ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ ዛሬ
የሚጀመር ሣይሆን ቀደምትም ነኝ፡፡ ልምዱን
በተግባር ሰርቼ አይቼዋለሁኝ፡፡ በ1990
ዓ.ም አካባቢ እኔ ነፍሱን ይማረው ስዩምና
ካሳሁን ተካ አብረን ሰርተን ጊዮርጊስን ቡናንና
ሌሎች ክለቦችን የጠቀሙ ብዙ ታዳጊዎችን
አፍርተናል፡፡ አሁን በዚህ ላይ በመስራት
እውቀቴን ማፍሰስ ነው የመረጥኩት፡፡