ስለ አሰልጣኞቻችን ሁሌ የሚነገረው አንድነት የላቸውም….አንድ ከሆኑም የሆነ የሚያጠቁት ሰው ሲኖር ነው የሚል አባባል ይደመጥ ነበር ምናልባት ሁለት ሶስት ጓደኛሞች የሚሆኑ አሰልጣኞች ላይጠፉ ይችላሉ ሲባል ኖሯል ይሄ ልዩነት.. አንዱ ላንዱ ያለው ተቃዋሚነትና ተቃራኒነት…ከሰአታት በፊት ሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል በተጠናቀቀው የብሄራዊ ቡድኑና የሊጉ ክለቦች አሰልጣኞች የምክክር መድረክ ላይ ላይመለስ የተደመሰሰ ይመስላል።
ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈው ቡድን የአሠልጣኞች ሀሳብን እንደ ግብአት ለመውሰድ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ የዋሊያዎቹ የአሰልጣኞች ቡድንን ጨምሮ 14 የሊጉ ክለቦች ዋናና ምክትል አሰልጣኞች ተገኝተዋል። የድሬዳዋ ከተማና የሰበታ ከተማ አሰልጣኞች ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስና ዘላለም ሽፈራው በውይይቱ ላይ ያልተገኙ ሲሆን እነሱም በምክትሎቻቸው ተወክለዋል
በውይይቱ ላይ ለካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው ቡድን የተሰጠው የ12 ቀን የዕረፍት ጊዜን አሰልጣኞቹ ውድቅ አድርገውታል። ቡድኑ ኢትዮጵያን እንደመወከሉ በአስቸኳይ የሊጉ መርሃግብር መቋረጥ አለበት የሚል አቋም ይዘዋል ከብዙ ጊዜያት በኋላ የታየው ይሄ አንድነት ለእግርኳሱ ትልቅ የለውጥ ተስፋ እንዳለ አመላካች ነው ተብሏል። ሲፈርስ ሲመሰረት የነበረው ማህበራቸውም ዳግም ሊያንሰራራ ጊዜው ሳይሆንም አልቀረም…
በውይይቱ ላይ የተገኘው የቀድሞው የዋሊያዎቹ የአሁኑ የባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ” የዝግጅት ቀኑ መጨመር አለበት በተለይ ቡድኑ ዝግጅቱን ከሀገር ውጪ አድርጎ በካምፕ ውስጥ በመገኘት ለውድድሩ ትኩረት መሠጠት አለበት” ሲል የመከላከያ አሰለልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ በበኩሉ “50 ግብ ቢቆጠርብንም 50 ግብ ብናስቆጥርም የእኛም እጅ አለበት ደስታውም መሸማቀቁም ለኛ አይቀርምና ለቡድኑ ጥሩ ዝግጅት ሲባል መቋረጥ አለበት” ብሏል። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ አሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት “ውድድሩ አሁኑኑ መቋረጥ አለበት ለሌላ ውድድርም ሲባል 2 ወር ሲቋረጥ አይተናል አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈንም ለዝግጅት የተሰጠው 12 ቀን ተገቢ አይደለም” ሲል የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማም ” በአንድ ግብ ስንሸነፍ ደስተኛ የነበርንበት ጊዜ ነበር አሁን ግን ከሽንፈት ወጥተን ወደማሸነፍ ዞረናል በራስ መተማመናችንም ጨምሯል ስለዚህ በአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ተፋላሚ እንድንሆን የዝግጅት ጊዜው መጨመር አለበት” ብሏል። የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እንደተናገረው ” ተጨዋቾቹ በጥሩ ፊትነስ ላይገኙ ሁሉ ይችላሉ ይህን ለማስተካከል ጥሩ የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋል” ብሏል።
- ማሰታውቂያ -
በአጠቃላይ የአሰልጣኞቹ የውይይት መድረክ በጥሩ አግባብ ተጠናቋል። ነገ ከሚጀመረው ሰባተኛ ሳምንት መርሃግብር በኋላ ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባል ውድድሩ እንዲቋረጥ በመስማማት ጥያቄያቸውን ለፌዴሬሽኑ ለማቅረብ ተስማምተው ወጥተዋል።
በቀጣይ ሊግ ኩባንያው ከዲ ኤስ ቲቪ ጋር ባለው ስምምነት መሠረት ለአሰልጣኞቹ የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል።