46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትናንትናው ዕለት ስድስቱም የክፍለ አህጉር የዞን ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓትሪስ ሞትሴፔ በተገኙበት ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ካፍ ለአባል ሀገራት ፌዴሬሽኖች የሚያከፋፍለውን ዓመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ከዚህ ቀደም ከነበረው በ150 ሺህ ዶላር ከፍ ማድረጉ ታውቋል።
ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው 250 ሺህ ዶላር ሲሆን በአዲሱ ማሻሻያ የአባል ሀገራት እግርኳስ ፌዴሬሽኖች በዓመት 400 ሺህ ዶላር ይከፋፈላሉ።
- ማሰታውቂያ -
በተጨማሪም የየክፍለ አህጉሩ የዞን ፌዴሬሽኖችም ከዚህ ቀደም ያገኙት ከነበረው 450 ሺህ ዶላር የ300 ሺህ ዶላር ጭማሪ በማድረግ 750 ሺህ ዶላር እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል።
ካፍ በተለይም በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸውን ስምንት የሚደርሱ የትኩረት አቅጣጫዎች አያይዞ ይፋ አድርጓል።
ከፌዴሬሽኖች ፣ መንግስታት እና የግል ሴክተር ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ፤ የተሻለ የአስተዳደር ስርዓት እና ተጠያቂነት ፤ ቀጣይነት ያለው ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም የቫር አካዳሚዎችን መገንባት ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በትምህርት እና ስልጠና የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት ፤ በትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ፤ የእግርኳስ ልማት ስራዎች በገንዘብ መደገፍ እና በሴት አሰልጣኞች ላይ በንቃት ለመስራት ማቀዱን ገልጿል።