ከተከፈተ 8ኛ ቀኑን በያዘው የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ራሱን እያጠናከረ ያለው መከላከያ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን አዲሱ አሰልጣኝ አድርጎ ለመቅጠር ተስማማ።
ከአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ውሉን እንደማያድስ ያስታወቀው መከላከያ ምክትሉ ዮርዳኖስ ዐባይን ጨምሮ ካሰናበተ በኋላ የተጨዋቾችን ዝውውር በመጪው አሰልጣኝ ጥቆማ ሲመርጥ መቆየቱ ታውቋል።
ከነዓን ማርክነህን ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በረከት ደስታን ከፋሲል ከነማ፣ ምንይሉ ወንድሙን ከወላይታ ድቻ በማስፈረም ራሱን ያጠናከረው መከላከያ ዛሬ ጠዋት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን አዲሱ አሰልጣኝ በማድረግ ለአንድ አመት አስፈርሞታል።
ባህርዳር ከተማና አዳማ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት የሰራው አሰልጣኝ ፋሲል በቀጣይ ሁለት አመታት የአብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ሁለተኛ ክለብ ከሆኑት ተወዳጅ ጥቂት ክለቦች መሀል አንዱ የሆነውን መከላከያን ወደ ውጤት ማማ እንዲያወጣ ተስፋ ተጥሎበታል።