በሊጉ የ21ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ሁለተኛ መርሀግብር ወላይታ ድቻ መቻልን 1 – 0 አሸንፏል ።
በወላይታ ድቻ በኩል በ20ኛው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በዮናታን ኤልያስ ምትክ ዘላለም አባቴን ተጠቅመዋል ። በመቻል በኩል ደግሞ በሳምንቱ ኢትዮጵያ መድኅንን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራ አንድ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በሳሙኤል ሳሊሶ እና ምንይሉ ወንድሙ ምትክ በረከት ደስታን እና እስራኤል እሸቱን ተክተው ገብተዋል ።
ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ የተደረገው እና ሁለቱን ከድል እና ሽንፈት መልስ የመጡ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረ ነበር ።
በአንፃራዊነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በ8ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል ለመፍጠር ችለው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
ይህ ኳስ ተመልሶ ከተገኘው የማዕዘን ምት የተሻገረው ኳስ ያገኘው ዳዊት ማሞ አክርሮ መምታት ቢችልም ቢንያም ገነቱ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በአጋማሹ ወላይታ ድቻዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት የመቻልን የኋላ መስመር ለመፈተን ያደረጓቸው ጥረቶች እጅግ ደካማ ነበሩ ።
በ26ኛው ደቂቃ ላይ ከነአን ማርክነህ ከበረከት ደስታ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ መቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋለም ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው ተስፋዬ አለባቸው ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በምንተስኖት አዳነ ተጨርፎ የግቡ ቋሚ የመለሰውን ኳስ ቶማስ ስምረቱ በግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ማግኘት ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ በሁለቱም በኩል ግብ አስቆጥረው ለመሸናነፍ ብርቱ ፉክክር ያደረጉበት ሳቢ የጨዋታ አጋማሽ ነበር ።
ነገር ግን በ55ኛው ደቂቃ ላይ የተፈጠረው የግሩም ሀጎስ እና የከነአን ማርክነህ ግጭት ምክንያት ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር ። በአጋጣሚውም ሁለቱም ተጫዋቾች በጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት አስተናግደዋል ።
በዚህም ግሩም ሀጎስ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ሲያመራ ከነአን ማርክነህ ለአስር ያህል ደቂቃዎች ጭንቅላቱን በመሸፈኛ አድርጎ ጨዋታውን ለመቀጠል ቢሞክርም በ65ኛው ደቂቃ ላይ በሳሙኤል ሳሊሶ ተቀይሮ ወጥቷል ።
በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ አዝማሚያዎች ሲታዩ የነበረ ሲሆን ስንታየሁ መንግስቱን ቀይሮ ያስገባው የጦና ንቦቹ ስብስብ በአንፃራዊነት አስፈሪ የግብ አጋጣሚዎች ን ለመፍጠር ችሎ ነበር ።
በ68ኛው ደቂቃ ላይም ቶማስ ስምረቱ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በስንታየሁ መንግስቱ ላይ በሰራው ጥፋት ወላይታ ድቻዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ።
ነገር ግን ቃልኪዳን ዘላለም አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ከፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት በኋላም አደገኛ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት የጦና ንቦቹ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል ።
መቻሎች በፈጣን ወደ ወላይታ ድቻ ሳጥን ይዘው ገብተው የነበረውን ኳስ ዳግም በሌላ የመልሶ ማጥቃት በዘላለም አባቴ አቀባይነት በስንታየሁ መንግስቱ ጨራሽነት የጦና ንቦቹ ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል ።
በቀጣዮቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በተለይም በመቻል በኩል ተደጋጋሚ የማጥቃት ሂደቶች ቢኖሩም አንዳቸውም ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል ደርሰው ቢንያም ገነቱን የፈተኑ አልነበሩም ።
በመጨረሻም በጦና ንቦቹ የ1 – 0 አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል ።
በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞ ሚያዝያ 23 በ9:00 ወላይታ ድቻ ከለገጣፎ ለገዳዲ ሲጫወቱ ረቡዕ ሚያዝያ 25 በ9:00 መቻል ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል ።