ባለፈው ዓርብ የተከሰቱ ሶስቱ ጉዳዮች…
*…..ክለቡ አሰልጣኝ ዘማርያምን አሰናበተ…
*…አሰልጣኙ ለፌዴሬሽኑ የፍትህ ያለህ አለ…
*…ዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰልጣኝ ዘማርያምን ወደስራ መልሳችሁ ደመወዙን ክፈሉ ሲል አዘዘ
- ማሰታውቂያ -
የድሬዳዋ ከተማና የቀድሞ አሰልጣኙ ዘማሪያም
ወ/ጊዮርጊስ አለመግባባት የአዲሱ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ሹመት የወቅቱ የእግርኳስ ቤተሰብ መነጋገርያ ሆኗል።
ሰኔ 30/2015 ድረስ ኮንትራት እያለው የድሬዳዋ ከተማ እግርኳስ ክለብ ቦርድ አሰልጣኝ ዘማሪያምን አግዶ ጉዳዩ ፌዴሬሽን ከደረሰና የፍትህ አካላት ከሁለቱ ወገኖች ምላሽ አግኝተው ውሳኔያቸው እየተጠበቀ ባለበት ሰአት ድሬዳዋ ያልተጠበቀ ውሳኔውን አሳልፏል።
ድሬዳዋ ከተማ ወደ ታዳጊ ቡድኑ ወርዶ እንዲሰራ አሰልጣኝ ዘማሪያምን ቢያዝም ውሌ የፕሪሚየር ሊግ እንጂ የታዳጊ ቡድን አይደለም በማለት አሰልጣኙ አሻፈረኝ በማለት አቋሙን ማሳወቁ ታውቋል።
ይህን ተከትሎ የድሬዳዋ ከተማ አመራሮች በታዳጊ ቡድኑ የስራ ገበታ ላይ አልተገኘም በማለት ሁለት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በማውጣት ባለፈው ዓርብ የካቲት 28/2014 ከክለቡ መሰናበቱን የሚገልጽ የስንብት ደብዳቤ ለአሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ መስጠቱ ይፋ ሆኗል።
አሰልጣኙ በዕለቱ ከክለቡ የተሰጠውን የስንብት ደብዳቤ በማያያዝ እስከ ሰኔ 30/2015 ድረስ ባለው ውል መሠረት ክፍያው እንዲሰጠው ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።
አስገራሚው ነገር በዕለተ ዓርብ ክለቡ አሰልጣኙን ባሰናበተበት አሰልጣኙም ተሰናብቻለሁ ውሌ ይከበረልኝ ባለበት ቀን ዲሲፕሊን ኮሚቴ የድሬዳዋ ከተማና የአሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስን አለመግባባት ከመረመረ በኋላ ለአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ፈርዷል።
ኮሚቴው የክለቡን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አሰልጣኙን እንዲመልስ ያልተከፈለውን ደመወዝ እንዲከፍለው ይህን በ7 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርግ ያ የማይሆን ከሆነ በውሉ መሠረት ሙሉ ክፍያው ተከፍሎት እንዲለያዩ ውሳኔው ካልተተገበረ ክፍያው በየቀኑ በ2 ፐርሰንት እንዲጨምር ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም አይነት ግልጋሎት እንዳያገኝና ከፕሪሚየር ሊጉ እንዲታገድ ወስኖ ለክለቡ ማሳወቁ ታውቋል።
ይህ የፍትህ አካል ውሳኔ ተወስኖም ቢሆን የክለቡ አመራሮች የቀድሞ የሀረር ቢራ፣ የዳሽን ቢራና ስሁል ሽረን አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን በአንድ አመት ኮንትራት ማስፈረማቸው አስገራሚ ሆኗል። ውሉ ያልተቋጨ አሰልጣኝ ውሉ ሳይፈርስ ወይም ሳይጠናቀቅ ሌላ አሰልጣኝ መሾምና ማጸደቅ ባለመቻሉ ክለቡም እስከ ሃሙስ ድረስ ይግባኝ ካላለ ወይም ውሳኔውን ተግባራዊ ካላደረገ የሚታገድ በመሆኑ ቀጣዮቹ ጊዜያት ለክለቡ አስጊ ሆኗል።
ድሬዳዋ ከተማ በአንደኛ ዙር 15 ጨዋታዎች ውጤት መሠረት በ16 ነጥብና 9 የግብ ዕዳ በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከወራጅ ቀጠናው በ2 ነጥብ ርቀት ላይ መገኘቱ መጪ ጊዜውን አስጊ አድርጎበታል። የሊጉ ሁለተኛ ዙር በአደማ ሲቀጥል ድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪ/ማርያምን ወላይታ ድቻን እንደሚገጥም መርሃግብሩ ያሳያል።