ሰላሳ ክለቦችን በሶስት ምድቦች እና በሶስት የተለያዩ ከተሞች ( ምድብ ሀ / ሆሳዕና ከተማ / ፤ ምድብ ለ / ሰበታ ከተማ / ፤ ምድብ ሐ / ጅማ ከተማ / ) ከፍሎ የሚያወዳድረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ የውድድር ግምገማ በዛሬው ዕለት በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል ።
መርሀ ግብሩን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ንግግር ተከፍቶ በሶስቱም ምድብ አመራሮች አጠቃላይ ሪፖርት ቀርቧል ። በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ የነበሩ በጎ ነገሮች ፤ የነበሩ ክፍተቶች እንዲሁም በቀጣይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ቀርበዋል ።
ከቀረቡት ክፍተቶች ውስጥ የመጫወቻ ሜዳዎች ጉዳይ ፤ የልምምድ ሜዳዎች እጥረት እና ርቀት ፤ የዳኞች ብቁነት ከጨዋታ በኋላ የሚቀርቡ ያልተናበቡ የጨዋታ ሪፖርቶች ፤ ከኮቪድ 19 ፕሮቶኮል ጋር በተያያዘ የታዩ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው ። በውድድር አመራሮች በሪፖርቶቹ ከቀረቡት ክፍተቶች እና በጎ ነገሮች በተጨማሪ ለነበሩ ችግሮች የተወሰዱ እርምጃዎችም ቀርበዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በመቀጠልም በአቶ ኢሳይያስ ጅራ መድረክ መሪነት በውድድሩ ከሚሳተፉ ክለቦች ተወክለው በመጡ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ፤ የታዩ ችግሮች እና መስተካከል ያባቸው ነገሮች በመድረኩ ተነስተዋል ። ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የሜዳ ችግሮች ፤ የዳኞች አቅም ጉዳይ ፤ በተከታታይ ጨዋታዎች መካከል ያሉ ቀናት መጣበብ ፤ ከደጋፊዎች ወደ ስታድየሞች መግባት ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተነተስተው በተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በአጠቃላይ በነበረው ሪፖርት ላይ እና በተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ እና በቀጣይ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ካነሱ በኋላ ግምገማው ተጠናቋል ።