የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ2016 የበጀት ዓመት ከ27 ሚልዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው በ16ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተገልጿል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት እንደተገለጸው ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 186 ሚልዮን 757 ሺህ 138 ብር ከ73 ሳንቲም ገቢ ተገኝቷል።
በአንፃሩ ለተለያዩ የፌዴሬሽኑ ስራዎች የወጣው ወጪ 214 ሚልዮን 90 ሺህ 240 ብር ከ93 ሳንቲም መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ከገቢ ወጪ 27 ሚልዮን 333 ሺህ 102 ብር ከ20 ሳንቲም ኪሳራ እንዳጋጠመው ተመላክቷል።
- ማሰታውቂያ -
በዓመቱ ለሴቶች ዋናው እና የዕድሜ እርከን ቡድኖች 51 ሚልዮን 758 ሺህ 919 ብር ከ08 ሳንቲም ወጪ ሲሆን ለወንዶች ዋናው እና የዕድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ በአጠቃላይ 44 ሚልዮን 789 ሺህ 623 ብር ከ90 ሳንቲም ወጪ ሆኗል።
በተለይም ለወንዶች ብሔራዊ ቡድኑ የወጣው አብዛኛው ወጪ በሜዳው ማድረግ የሚገባውን ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ በማድረጉ የተመዘገበ መሆኑ ተገልጿል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በጉባኤው እንዳሉት ከሆነም ብሔራዊ ቡድኑ ሀገሩ ላይ ጨዋታዎችን ማድረግ ቢችል ኖሮ ቢያንስ ከ22 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ይቻል ነበር።