“በምርጫው ባልመረጥም የትም አልሄድም የፌዴሬሽኑ አባል ባልሆን ወደ ፊፋ መግባት እችላለሁ”
ኢ/ር ቶኪቻ አለማየሁ
/ ዕጩ ፕሬዝዳንት /
👉” ኢትዮጵያ በካፍና በፊፋ ቦታ የማግኘት የአመራር ድርሻና ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራት እጥራለሁ” ሲሉ ኢንጂነር ቶኪቻ አለማየሁ ተናገሩ።
ኢ/ር ቶኪቻ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ
“120 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ በካፍና ፊፋ አንድም ቦታ የላትም ጎረቤት ሀገር ጂቡቲ ግን ተወካይ አላት ይሄ የሆነው እርስ በርስ የምንገፋፋ እንጂ የምንደጋገፍ ባለመሆኑ ነው ጠላት ሲመጣ እንጂ የምንደጋገፈው በሌላ ጉዳይ አንደጋገፍም ከእግርኳሱ ይሄ መገፋፋት እንዲጠፋ እሰራለሁ” ሲሉ ተናግረዋል
“ጋዜጠኞችና ደጋፊዎች የኢትዮጵያን እግርኳስ መሸጥ አለባቸው አቅሙ የነሱ ነው” ያሉት ኢ/ር ቶኪቻ “እኔ የማንም ወገን አይደለሁም የጋዜጠኛ የአሰልጣኝ የፌዴሬሽኑ የክለቦችም አይደለሁም እኔ መሃል መሆን እችላለሁ ቡድንተኝነት ከኳሱ እንዲጠፋ በርትቼ እሰራለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
“የክልል ፌዴሬሽኖች ካላደጉ አዲስ አበባ ያለው ፌዴሬሽን ሊያድግ አይችልም ለውጥም አይመጣም እኔ ፕሬዝዳንት ስለሆንኩም የማመጣው ለውጥ የለም ክልሎች ለብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጥሩ ዕይታ የላቸውም ይሄ መስተካከልና በጋራ ተጋግዘን ልንሰራ ይገባል” ያሉት ዕጩው ፕሬዝዳንት “ተፈትኖ ያለፈ አመራር ቢመጣ ደስ ይላል እስማማለሁ ግን እንዴት ይምጣ ..? ኳሱን የሚያውቁት አቶ ገዛኸኝ ወልዴኮ አሁን የሉም እኔ ደፍሬ የመጣሁት እጄን ከምጠቁም የለውጡ አካል ልሁን ብዬ ነው ከተመረጥኩ ዋንጫ ለማሸነፍ አራት አመት ሙሉ እጠብቃለሁ ብዬም አላስብም ባሸንፍ በዚህ መንገድ ያሉትን ሙሉ ክፍተቶችን የምደፍነው ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ ባለው ችግር ዙሪያ የተናገሩት ኢንጂነሩ “ፖለቲከኛ ወታደር ተጨዋች መሆን አልችልም ነገር ግን ሀገሬን በኳሱ መጥቀም እፈልጋለሁ ብመረጥ ከፌዴሬሽኑ የምወስደው ጥቅማ ጥቅም ገንዘብ የለም ኳሱ ላይ የበረታው ዘረኝነት መቆም አለበት ብሄሮች ትላንት ነበሩ ዛሬም አሉ ነገም ይኖራሉ ማጥፋት የምንችለው ዘረኝነትን ነው ይሄን ለማቆም የምችለውን አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሃላፊነቱን ከወሰድኩ የዛሬ አመት ይሁን የዛሬ አራት አመት ዋንጫ እንወስዳለን አልልም በርግጠኝነት ግን ከኔ ቀጥሎ የሚኖረው ፕሬዝዳንት በድፍረት ዋንጫ እወስዳለሁ እንዲል ለማድረግ እጥራለሁ ያሉት ኢ/ር ቶኪቻ “በመጪው አራት አመታት እኔ ፊፋ ውስጥ የመግባት ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ግን ወደ ካፍ እንዲገቡ እጥራለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በታክሲዬና በፌዴሬሽኑ ዙሪያ ስለነበረው ልዩነት የተጠየቁት ኢንጂነር “እኛ ነን በራሳችን ተነሳሽነት የጠየቅነው ተስማማንና ንግግር ተጀመረ ከማርኬቲንግ አንጻር ካየነው ለክለቦቹ ስፖንሰር ቢደረግ ይሻላል በኛ በኩል ቅድመ ሁኔታ አቅርበናል በውላችን መሠረት አላደረጋችሁም ብለን ለፌዴሬሽኑ ሶስት ደብዳቤ ልከናል ምላሽ እየጠበቅን ነው” ነው ሲሉ ተናግረዋል። ወደ ካሜሩን በነበረው ጉዞ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት ወደ አንድ ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎ የባህል ልብስ ተሰርቶ ሁሉም አባላት ለብሰው ሄደዋል እሱንም እኛ ፈቅደን ያደረግነው ነው ነገም እንቀጥላን ዋሊያዎቹ አገር ወክለው እንደመሄዳቸው ሁሌም ከጎናቸው ናቸው ለደጋፊ የተሰራ ወደ 700 ማሊያ ታክሲዬ ተብሎ የተሰራ ማሊያ ሳይሸጥ ቆልፈው ሄደዋል ይሄም ያሳዝናል ሜዳውን በተመለከተ የቋንቋ ችግር ካልሆነ በስተቀር አመራሮቹ የባህርዳር ስታዲየም ጨዋታውን ቀን ላይ እንዲያደርግ ጫና አለማሳደራቸው ያሳዝናል ዶክተር አሸብርኮ ሜዳው ታግዶ ሌላ ቦታ ላይ አምጥቶ እንዲጫወቱ አድርጓል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጉባኤው ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን እንዴት አዩት የተባሉት ኢንጂነሩ ” አመራሩ ጉባኤው ረብሻለሁ አለ እንጂ ጎንደርን እረብሻለሁ አላለም በአዲስ አበባ በሚደረገው ምርጫ ላለመረበሹ ምን ዋስትና አለ…? ስሜታዊ ውሳኔ እንደተወሰነ ነው የሚገባኝ.. ግለሰብ እንደፈለገ የሚሆነው ቤቱ ውስጥ ነው ከዚያ ውጪ ተቋማዊ ጥበቃ ማድረግ እየተቻለ ቦታ መለወጥ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢንጂነሩ በቀጣይ ” በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በክልል እግርኳስ ፌዴሬሽኖችና በክለቦች ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፤ ያሉት ስታዲየሞች በካፍና በፊፋ ስታንዳርድ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲጠናቀቁ ማድረግ፤ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን ቀይሶ ገቢን ማሳደግ፤ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በብዛትና በጥራት ማፍራት፤ በውጪ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ግንኙነት መፍጠር ፤ የእግርኳስ ማበረታቻ ሰርዓትን መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ፤ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና ክለቦች የትምህርት ቤቶች እግርኳስ አካዳሚዎች የስልጠና ውድድሮችን ማስፋፋት ላይ እንደሚሰሩ አሳውቀዋል።
ኢ/ር ቶኪቻ ስልጣን ከያዙ ሊሰሯቸው ያሰቡትን ከዘረዘሩ በኋላ ሌሎቹን ስትራቴጂዎች ፕሬዝዳንት ሆኜ ከተመረጥኩ በኋላ በቀጣዩ ማክሰኞ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።