አለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት
ጠቅላላ ጉባኤው እንዲቀጥል ፈቀደ
,….. “ዋና ጸሀፊነት ህይወቴ አይደለም”
*….. “የደብረዘይቱ ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴል ውስጥ
የሚካሄደውን ጨምሮ የምርጫ ድራማዎች
ቀጥለዋል ”
አቶ ባህሩ ጥላሁን
/የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ/
- ማሰታውቂያ -
አለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ በተያዘለት መርሃግብር እንዲቀጥል ፈቀደ።
አስመራጭ ኮሚቴው የእግርኳስ ፌዴሬሽኑን ደንብና የምርጫ ኮዱን ጥሶ ከምርጫ ውጪ አድርጎኛል የኮሚቴው አባላትም ገለልተኛ አይደሉም በማለት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ያቀረቡትን ክስ የመረመረው ካስ የፌዴሬሽኑን ምላሽ ከሰማ በኋላ ጉባኤው እንዲቀጥል መፍቀዱን ፌዴሬሽኑ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል። ካስ የጉባኤውን መካሄድ ይፍቀድ እንጂ በቀጣይ በሚኖሩ የሰነድ ክርክሮች ሂደቱ ታይቶ አቶ ገዛኸኝ በክሱ የሚረታና የጉባኤው ውጤት የሚሰረዝ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ሙሉ ሀላፊነቱን የሚወስድ እንደሚሆን ይገመታል።
በሌላ በኩል ስለ 13ኛው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅትና የተከናወኑ ተግባራት ፌዴሬሽኑ በዋና ጸሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን አማካይነት ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥቷል። በዚህ መግለጫ ዋና ጸሀፊው ቦታቸውን የማጣት ስጋት እንደሌለባቸው ያስረዱት ” ዋና ጸሀፊነት ህይወቴ አይደለም” በማለት ነው። አቶ ባህሩ ሀላፊነታቸውን በሚገባ እንደሚወጡና እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ስራቸውን በገለልተኝነት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
ዋና ጸሃፊው ስም ጠቅሰውና ያለውን እውነት በዝርዝር ባይገልጹም ከእሁዱ ምርጫ ጋር ተያይዞ የደብረዘይቱ ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ጨምሮ በየሆቴሉ በድብቅ የተለመዱ ምርጫ ተኮር ድራማዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ታማኝ ምንጮች ግን በጉባኤው ድምጽ የሚሰጡ የተወሰኑ አካላት ትላንት ምሽት በኮስትር መኪና ተጭነው ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማደራቸውና በአንደኛው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሙሉ ወጪ ተችሎ ድምጻቸውን ለመግዛት መሞከሩ ታውቋል። 137 ድምጽ መሃል የትኛው በተሻለ ሀሳብ እንደሚመርጥ የትኛው ድምጹን ለመሸጥና ከምርጫው በፊት 20ሺህ ብር ከምርጫው በኋላ 20 ሺህ ብር ለመቀበል እንደተስማማ ባይታወቅም የተለመደው ምርጫ ተኮር የድምጽ ሽያጭ መቀጠሉ እየተነገረ ነው ። በቶሚ ሆቴል ውስጥ በኢትየዮጵያ እግርኳስ ከፍተኛ ስራ የሰሩ ባለሙያዎች መካተታቸውና በምርጫው ላይ የአንዱ ወገን ደጋፊ ሆነው መታየታቸው አስገራሚ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነገና ከነገ በስቲያ የሚካሄደው ይኸው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 137 ድምጽ የሚጠበቅ ሲሆን ባለው ስታስቲክስ መሰረት ምርጫው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው አራት ክልሎች ሆነዋል። ኦሮሚያ ክልል በ35 ድምጽ፣ ደቡብ ክልል በ25 ድምጽ፣ አዲስ አበባ ከተማ በ23 ድምጽ እንዲሁም አማራ ክልል በ21 ድምጽ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል። ሲዳማ ክልል በ5 ድምጽ፣ ድሬዳዋ ከተማና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በእኩል አራት አራት ድምጾቾ ፣ አፋር ክልል፣ ሶማሌ ክልልና ሀረሪ ክልል እኩል ሶስት ሶስት ድምጽ አጠቃላይ ማህበራት ደግሞ 8 ድምጾችን ይዘዋል።
በድምጻቸው የተሻለውን የሚመርጡ መራጮችና ድምጻቸውንና ህሊናቸውን በገንዘብ ጥቅም የሚሸጡ የኢትዮጵያ እግርኳስ መራጮች መሃል የሚደረገው ትግል አጓጊ ሆኗል።