የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ውላቸውን ለማራዘም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በዛሬው ዕለት ስምምነት ፈፅመዋል።
በ2013 ዓ.ም ብሔራዊ ቡድናችንን በመረከብ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በስራ ላይ የቆዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቆይታቸው ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከስምንት ዓመት በኋላ የተመለሰ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በአልጄርያ ለሚከናወነው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ የውድድር ተሳትፎ አሳክቷል። አሰልጣኙ ውላቸው መጠናቀቁን ተከትሎም ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት (እስከ መስከረም 2017) በዋና አሰልጣኝነት እንዲቀጥሉ በዛሬው ዕለት የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ከውል ማራዘም ጋር የተያያዙ ዝርዝሮች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ማለፉን የተመለከተ ማብራርያ ሰኞ መስከረም 9/2015 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከቀኑ 9፡00 ላይ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ይሆናል።