*…. ወላይታ ድቻ … ወደ ድቻ ስፖርት ክለብ..?
በ2015 የውድድር አመት የብሄርና የሃይማኖት ስያሜ ያላቸው ክለቦች ተቀባይነት የላቸውም የሚለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ተግባራዊ የመደረጉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።
ሀትሪክ ባገኘቾው መረጃ በፕሪሚየር ሊጉ በከፍተኛ ሊግና አንደኛ ሊግ የሚገኙ ወደ 20 የሚጠጉ ክለቦች የስማቸውን ስያሜ እንዲያስተካክሉ የተነገራቸው ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ከሚገኙ 16 ክለቦች መሃል ሶስቱ ወላይታ ድቻ ፣ ሀድያ ሆሳዕናና ሲዳማ ቡና ደብዳቤ ቢደርሳቸውም ለውጥ ሳይታይ ሊጉ ትላንት መጀመሩ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በተደጋጋሚ የተናገሩትና የግድ ተፈጻሚ መሆኑ አይቀርም በማለት የሰጡት ማሳሰቢያ ተግባራዊ ሳይደረግ ሊግ ኩባንያው ያለስያሜ ለውጡ ውድድሩ እንዲጀመር ማድረጉ ጥያቄ አስነስቷል። ይህም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሶስቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ላይ መመርያውን ተፈጻሚ ካላደረገ ቀሪዎቹን 17 ክለቦችን የማስገደድ አቅሙ ላይ ጥያቄም እንዳይነሳ ተሰግቷል።
- ማሰታውቂያ -
የሊግ ኩባንያው በጉዳዩ ዙሪያ ለሀትሪክ እንደገለጸው ፌዴሬሽኑ ለሶስቱ ክለቦች ስም ይቀይሩ ብሎ የላከው ደብዳቤ በግልባጭ የደረሰው መሆኑ ገልጾ ነገር ግን ምዝገባ የተደረገው ከሃምሌ 4 እስከ ሀምሌ 16 በመሆኑ ነሀሴ ላይ የወጣውን ደንብ አስገድዶ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን ገልጿል። ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ የስም ለውጡ ሲወራ እንደነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስን አለማካተቱና ስም ቅየራው እንደማይመለከተው ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ፈጣን ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ግን ውሳኔው መተግበሩ አይቀርም ሲል ጠንካራ አቋሙን አሳውቋል ለሀትሪክ ምላሹን የሰጠው ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ መመሪያ ሰጥተናል በሊግ ኩባንያ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተን ማብራሪያና ግንዛቤ በመስጠት ውሳኔው የግድ ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስበናል አሁንም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነግረናል ጉዳዩ ወደኋላ የማንልበት ውሳኔ ነው ሲል ምላሹን ሰጥቷል።
ይህ ዘገባ ትላንት ከተጠናከረ በኋላ ዛሬ ከቀትር በኋላ በተሰማ ሌላ መረጃ ከሶስቱ በብሄር ስም ከሚጠሩ ክለቦች መሃል አንዱ ነው የተባለው ወላይታ ድቻ መመሪያውን ተቀብሎ ስያሜውን “ድቻ ስፖርት ክለብ” ብሎ መለወጡን ፌዴሬሽኑ ሊግ ኩባንያውን ጠቅሶ በፔጁ ላይ ይፋ አድርጎታል።