የተለያዩ የውድድር አመራሮች ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ በዳኝነት እና በጨዋታ ታዛቢነት መመደባቸው ተገለፀ፡፡
ኦሎምፒክን ጨምሮ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮችን በዋና ዳኝነት እየመራ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ በዛሬው እለት ሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት በቤኒና ማርቲረስ ስታዲየም በኳታር አስተናጋጅነት በ2022 ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉትን የሊቢያ እና የጋቦን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመራ ሲሆን በዚሁ ጨዋታ ኢትዮጵያዊ ኢንተርናሽናል ዳኞች ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሳሙኤል ተመስገን በ1ኛ ረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው በ2ኛ ረዳት ዳኝነት እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በ4ኛ ዳኝነት ጨዋታውን የሚመሩት ይሆናል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ
በኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ካኘ አንዱ በሆነው የደቡብ ሱዳኑ አትባራ እግር ኳስ ክለብ እና የሱዳን አል ሃሊ ሜሮዌ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የምትመራው ይሆናል፡፡ ይህው ጨዋታ በሱዳን አል ኦቤድ ስታዲየም መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት የሚደረግ ሲሆን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከኢትዮጵያዊያን የሙያ አጋሮቿ ጋር በ1ኛ ረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሳሙኤል ተመስገን ፣ በ2ኛ ረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ ብሩ እንዲሁም በ4ኛ ዳኝነት /ተጠባባቂ/ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ ከብቸኛዋ ሴት ዋና ዳኛ ጋር በጋራ ጨዋታውን ይመራሉ፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ እያካሄዳቸው በሚገኙ ውድድሮች በርካታ የኢትዮጵያ ዳኞችን በመመደብ ዳኞቻችን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎአቸውን በማድረግ ላይ ሲሆኑ የሱዳኑ ሄይ አልዋዲ ከ ሊቢያው ሃሊ ትሪፖሊ እግር ኳስ ክለብ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ በ1ኛ ረዳት ዳኝነት ክንዴ ሙሴ፣ በ2ኛ ረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሸዋንግዛው ተባበል፣ እንዲሁም በ4ኛ ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን መስከረም 2 ቀን 2014 ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት በሱዳኑ አል ኦቢድ ኦቢድ ስታዲየም ጨዋታውን እንዲመሩ ተደልድለዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
በተጨማሪም ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው በ1ኛ ረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ይበቃል ደሳለኝ በ2ኛ ረዳት ዳኝነት እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ በ4ኛ ዳኝነት የጅቡቲው አስ አርታ ሶላር 7 ከኬኒያው ቱስካር እግር ኳስ ክለብ ጋር የሚያደርጉትን የካፍ የክለብ ሻምፒዮና ወደ ጅቡቲ ተጉዘው በኢትዮጵያን አዲስ ዓመት መስከረም 1 ቀን 2014 ጨዋታ ይመራሉ፡፡
በዓለም አቀፋ የእግር ኳስ መድረክ ሀገራችንን ወክለው ከሚሳተፋ ዳኞች በተጨማሪ በኮሚሽነርነት እና በኮቪድ 19 ኦፊሰርነት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ዋ ፀሐፊ እና የካፍ ኢንስትራክተር የሆኑት አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ በሱዳን አል ሃሊ ሜሮዌ እና በደቡብ ሱዳኑ አትባራ እግር ኳስ ክለብ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ በኮሚሽነርነት እንዲመሩ እንዲሁም የካፍ ኢንስትራክተር የሆኑት አቶ ግዛቴ ዓለሙ የሶማሌው ሞቋዲሾ ሲቲ ክለብ ከ ሩዋንዳው ኤፒአር እግር ኳስ ክለብ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በኮሚሸነርነት በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕክምና ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር በረከት ቦጋለ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ውድድሮች አገራችንን ወክለው ከኡጋንዳው ኡጋንዳ ሬቬኒዩ አውቶሪቲ ስፖርት ክለብ ጋር የካፍ ክለብ ሻምፒዮን ጨዋታውን ለሚያደርገው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የኮቪድ ኦፊሰር በመሆን በሙያቸው እንዲያገለግሉ መመደባቸውን ካፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ዝርዝር ገልጿል፡፡