የባህር ዳር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ከባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የካፍ ”C License” የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ መስፈርቱን ያሟሉ 24 ሰልጣኞች ከጥቅምት 12 ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከቀናት በፊት አርብ አጠናቀዋል።
ስልጠናው በኢንስትራክተር ሰላም ዘርአይ ፣ በኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማሪያም እና በካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ አማካኝነት ሲሰጥ መቆየቱም ይታወቃል።
በመዝጊያ ፕሮግራሙ ዕለትም ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት ምስጋና አቅርበው የክልሉን የእግር ኳስ ስፖርት ለማሳደግ ተመሳሳይ ስልጠናዎች በሌሎች የክልሉ ከተሞች ለመስጠት የሚያስችል ስራዎች እንደሚስራ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ ገልፀዋል።