ከቀናት በፊት በተከናወነው የኢትዮጵያ ቡና እና የወላይታ ዲቻ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃም ጨዋታ ላይ የተከሰተዉን የዲሲፕሊን ግድፈት ተከትሎ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴዉ በዕለቱ በተካሄደው ጨዋታ ላዬ ጨዋታውን የመሩት የጨዋታ አመራሮችና የውድድር አመራሮች ያቀረቡትን ሪፖርት አይቶ በመርመር ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
በዚህም የወላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብን መለያ በለበሱ ደጋፊዎች በድምሩ 840 የመቀመጫ ወንበሮች በመሰባበራቸዉ እና በመፀዳጃ ቤቶች ዉስጥ የሚገኙ የተለያዩ ንብረቶች ላይ ውድመት ማድረሳቸዉን ተከትሎ ክለቡ በመመሪያዉ መሰረት የሶስት መቶ ሀምሳ ሺ ( 350,000.00 ) ብር ቅጣት ሲጣልበት ፤ በተጫዋቾች ደግሞ በጨዋታዉ 106ኛዉ ደቂቃ ላይ የዕለቱ ዋና ዳኛ ኳስ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ ፍፁም ቅጣት ምት የሲጡ ሲሆን ይሄንንም ተከትሎ የዳኛን ዉሳኔ ባለመቀበል ዳኛዉ ላይ ከበባ በመፈፀም ጨዋታዉ ለ7 ያክል ደቂቃ እንዲቋረጥ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ቢኒያም ፍቅሬ እና ብስራት በቀለ የ20,000.00 ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልባቸዉ ፤ ኬኔዲ ከበደ ፣ ናትናኤል ናሲሮ ፣ አዛርያስ አቤል ደግሞ የ10,000.00 ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አማካኝነትም 194 ወንበሮች እና የተለያዩ የመፀዳጃ ቤት ንብረቶች ዉድመት ስለደረሰባቸዉ ክለቡ 100,000.00 ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል።
በክለቦቹ ደጋፊዎች ጉዳት ደርሶባቸዉ ከጥቅም ውጭ የሆኑትን ንብረቶችንም ክለቦቹ በራሳቸዉ ወጪ እንዲያስገነቡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።