የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአሁን ሰዓት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በዓመቱ የተሰሩ ዋነኛ ተግባራት እና ያገጠሙ እክሎችን ለመድረኩ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃውን የጠበቀ ስታድየም ባለመኖሩ ከሀገር ውጪ ወጥቶ ለመጫወት መገደዱን በማንሳት መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ በበጀትም እንዲደግፍ ጠይቀዋል።
አክለውም ብሔራዊ ቡድኑ ሀገሩ ላይ ጨዋታዎችን ማድረግ ባለመቻሉ ስፖንሰሮች እየሸሹ በመምጣታቸው ፌዴሬሽኑ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን ገልፀዋል።
- ማሰታውቂያ -
ይህ ሁኔታ መፍትሔ ካላገኘ ፌዴሬሽኑ ዋናው እና ሌሎች የዕድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበትን በርካታ ውድድሮች ለመሰረዝ ይገደዳል ብለዋል።
በክልሎች ያሉ ስታድዮሞች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ፌዴሬሽኑ የባለሙያዎች ድጋፍ ቢያደርግም በአንዳንድ ቦታዎች ሀሳቦችን አለመቀበል እና አለፍ ብሎም በጥርጣሬ የማየት ነገር ተስተውሏል ሲሉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል።