የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ15፣ 17 እና 20 ዓመት በታች የዕድሜ እርከኖች ወጣቶችን በማሰልጠን እና ለብሔራዊ ቡድኖቻችን፤ አልፎም ለታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ገበያ ለማብቃት በማሰብ የሚገነባው የወጣቶች ብሔራዊ አካዳሚ ፕሮጀክት ይፋ የሚሆንበት እና በአካዳሚው አስተዳደር ላይ በጋራ ለመስራት ከጀርመን ድርጅት ጋር የስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓት ፕሮግራም በዛሬዉ ዕለት ሰኞ ህዳር 13/2014 ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ በይፋ ፕሮግራሙን ያስጀመሩ ሲሆን በመቀጠልም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አጠቃላይ ስለ ስምምነታቸዉ ገለፃ አድርገዋል በገለፃቸውም :-
ከ3 point National Academy Project ጋር የፈፀሙት ስምምነት ለአራት አመታት ቆይታ የሚኖረዉ ሲሆን በየአምስት አመቱ ዉላቸዉ የሚታደስም ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ ጥሩ ጥሩ የሚባል ብቃት ያላቸዉ ወጣት ተጫዋቾች ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአካዳሚ በመታቀፍ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ዘመናዊ ስልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል።
በተያያዘም እንደስምምነቱ ከሆነ ከየአካባቢው ተመርጠዉ የሚመጡትን ወጣት ተጫዋቾች የምግብ ፣ የጤና ፣ የትምህርት እና የመሳሰሉትን ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪም ለታዳጊዎቹ የአሰልጣኝ ወጪዎችን 3point የተሰኘዉ የትዉልደ ኢትዮጵያዊዪ ቴዎድሮስ ሳሙኤል ድርጅት ሙሉ ወጪዉን የሚሸፍን ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በኩል ደግሞ አስፈላጊውን የቦታ እንዲሁም አካዳሚውን ለመገንባት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሲሆን የውጪውን ግማሽ አራት ሚሊዮን ብርም እንደሚሸፍኑ ተገልጿል። አጠቃላይ የግንባታው ወጪም ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ተነግሯል።
- ማሰታውቂያ -
በመቀጠልም የፕሮጀክቱ መስራች እና ባለቤት ትዉልደ ኢትዮጵያዊዩ ቴዎድሮስ ሳሙኤል ታዳጊ ተጫዋቾችን ከየክፍለሀገሩ በመመልመል ወደ አዲስ አበባ በማምጣት በሚገነባው አካዳሚ በማቀፍ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ስልጠናዎችን በመስጠት ታዳጊዎቹን በማብቃት ወደ አዉሮፓ ሊጎች በሚገኙ ክለቦች የሚጫወቱበትን ዕድል መፍጠርን ግብ አድርጎ በተነሳው ፕሮጀክቱ ላይ የተወሰኑ ሀሳቦችን በስፍራው ለነበሩ ጋዜጠኞች ገለፃ አድርጓል።
ወላጅ እናት እና አባቱን በማመስገን ንግግሩን የጀመረው ቴዲ በጀርመን ሀገር ያገኘዉን ዕዉቀት እና ልምድ ተጠቅሞ ለትዉልድ ሀገሩ ታዳጊዎች ዕድልን በመፍጠር ወደ አዉሮፓ ወጥተዉ የሚጫወቱበትን ዕድል ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን በቻለዉ አቅም የሀገሩን እግርኳስ ለማገዝ እና ለመርዳት ከድሮ ጀምሮ ትልቅ ፍላጎት እንደነበረዉ ገልጿል። በተጨማሪም ታዳጊዎቹን የሚያሰለጥኑትን ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች የብቃት ደረጃ ያሻሽላል የተባለ ስልጠና ከሀገረ ጀርመን በመጡ አሰልጣኞች እንደሚሰጥ ተገልጿል። በተያያዘም የዚህ ፕሮጀክት መስራች የቴዎድሮስ ሳሙኤል ልጅ ዴቪድ ሲልከ በጀርመኑ ታዋቂ ክለብ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ለጀርመን ብሔራዊ ቡድንም በተለያዩ የእድሜ እርከኖች መጫዎት ችሏል። ተጫዋቹንም ለአባቱ ሀገር ዋና ብሔራዊ ቡድን ለዋልያዎቹ እንዲጫወት ምክክሮች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጋር መደረጋቸዉን አብራርቷል።
በመጨረሻም በሚቀጥለው አንድ ወር የአካዳሚዉ ግንባታ እንደሚጀመር የተገለፀ ሲሆን በዕለቱም በቅርቡ የሚገነባዉ አካዳሚው ዲዛይን ለዕይታ በቅቷል።
በመቀጠልም በስፍራው ከነበሩ የሚዲያ አካላት የተወሰኑ ጥያቄዎች ተነስተዉ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዉ የፌርማ ስነስርዓቱ ተካሂዶ በይፋ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።