“ለጎንደር ህዝብና ለፋሲል ደጋፊ ያለኝ ፍቅር የተለየ ነው፤ፈልጌ ሳይሆን ተገፍቼ ነው የወጣሁት”
እንየው ካሳሁን /ድሬዳዋ ከተማ/
ለድሬዳዋ ከተማ የፈረመው እንየው ካሳሁን ከምወደው ክለብ የወጣሁት ተገድጄ ነው ሲል ተናገረ።
ተጨዋቹ በተለይ ለሃትሪክ እንደተናገረው ከምወደው ክለብ እወጣለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም ነበር ብሏል። “የቀረበልኝ ደመወዝ ከጠየኩት ጋር ባይገናኝም ክለቡን ስለምወደው ተስማምቻለሁ በቅድሚያ ክፍያ መጠን ላይም አልተከራከርኩም ነገር ግን የቅድሚያ ክፍያውን የምንሰጥህ ጥቅምት ወር ላይ ነው አሉኝ እሺ ለጥቅምቱም ቼክ ጻፉልኝ ስላቸው አንጽፍልህም እመነን ሲሉኝ ተበሳጨሁ ለሌላው የፊርማ ክፍያ እየሰጡ እኔን ለምን ይከለክሉኛል? ለዚህ ነው እንደማልፈለግ የገባኝ”ሲል ተናግሯል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በበኩሉ “እንደምንፈልገውማ ያውቃል የቦርድ አባላቱና ኮሚቴው ከአንዴም ሁለቴ ያናገሩት ለዚያ ነው እኔና የቡድን መሪው አቶ ሀብታሙ ዘዋለ ፌዱሬሽን ሆነን ለፊርማ ሁለት ቀን ስንጠብቀው መጣሁ እያለ ቀርቷል አልተገኘም ይሄ መቀጠል ስላልፈለገ ይመስለኛል በቦታው ተመራጭ የነበረው ሰዒድ ሀሰን ነበር በመጎዳቱ እንየው እንዲተካው ተደርጎ ጥሩ አቋሙን አሳይቷል በፋሲል ከነማ የገጠመው ስኬትን ማሰብም ነበረበት” በማለት ከፋሲል የለቀቀው መቀጠል ባለመፈለጉ ነው የሚያስብል አስተያየቱን ሰጥቷል።
እንየው ካሳሁን ግን የአሰልጣኙን ሃሳብ ያስተባብላል “ትክክል አይደለም ከክለቡ አመራሮች ጋር በውል ማደስ ዙሪያ ሳንስማማ ፌዴሬሽን እየጠበቅንህ ነው ናና ፈርም ማለታቸው ተገቢም አልነበረም ክርክር ላይ ባለ ጉዳይ ገና ሳንስማማ የእነሱ እኔን ፌዴሬሽን መጠበቅ ትክክል አልነበረም ያለው እውነት ይሄ ነው” ብሏል። “ድሬዳዋ ከተማዎች ሙሉ ክብር ሰጥተው እንዴት እንደሚፈልጉኝ አሳይተው አስፈርመውኛል እነሱንም አመሰግናለሁ ለድሬዳዋ ከተማ የምችለውን ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ” ያለው እንየው ካሳሁን አጽንኦት የሰጠው ለጎንደር ህዝብና ለፋሲል ደጋፊዎች ስላለው ፍቅር ነው። “ለጎንደር ህዝብና ለፋሲል ከነማ ደጋፊ ትልቅ ክብርና ፍቅር አለኝ መቼም ከልቤ አይወጡም ለዚህ የደረስኩት እነሱ ከጎኔ በመሆናቸው ነው ለሁሌውም መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ ስለ እውነት ለመናገር ለጎንደር ህዝብና ለፋሲል ደጋፊ ያለኝ ፍቅር የተለየ ነው፧ ፈልጌ ሳይሆን ተገፍቼ ነው የወጣሁት ይህን እንደሚረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።
በዚህ ቅሬታ ዙሪያ ከሃትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ.. “እንየው ካሳሁን ውሉን እንዲያድስ ለማድረግ ሞክረን አልተሳካልንም ነገር ግን ክለቡ ከተጨዋች በላይ ነውና ጉዞው ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አቢዮት እንዳሉት ” ከበጀት መዘግየትና መፍጠን ጋር ተያይዞ አንዳንዴ እንዲህ አይነት ነገር ሊከሰት ይችላል እስካሁንም በጀት አልተለቀቀልንም ነባር ተጨዋቾቻችን ውል ሲያድሱ ቼክ ጠይቀውን አያውቁም እሱ መጠየቅ ግን መብቱ ነው ያም ሆኖ መስማማት ባለመቻሉ ክለቡን ተሰናብቷል ለሌላው ቼክ እየሰጡ ለኔ ለምን ከለከሉ ላለው ማንኛውም ተጨዋች ራሱን ወክሎ እንጂ ሌሎችን እያየ እንቢ ወይም እሺ ማለት ተገቢ አይመስለኝም እንደ ተጨዋች ሊተካ የሚችልና በቀላሉ የማይተካ ተጨዋች ሲኖር የምናቀርበው መደራደሪያና የምናስተላልፈው ውሳኔ ሊለያይ ይችላል” ሲሉ መልሰዋል።
“በክለባችን የማይጣስ መርህ አለ በኛ በኩል የማናደርገውን ቃል አንገባም የተናገርነውን ደግሞ እንፈጽማለን ባለፉት 5 አመታት ጠንካራ ሆነን የሊጉንም የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያነሳው በሻምፒየንስ ሊግም ይሁን በኮንፌዴሬሽን ካፕ የምንካፈለው በዚህ ጥንካሬያችን ነው” በማለት ስራ አስኪያጁ አቶ አቢዮት ብርሃኑ ለሃትሪክ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።