የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር –
በጎንደር የሚካሄደው የፌዴ. ጠቅላላ ጉባኤ
እንዲታገድ ለመደበኛ ፍ/ቤት ክስ መሠረተ
*….የክሱ ምክንያት ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ
ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም መባሉ ነው
የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር በጠቅላላ ጉባኤው የአባላቶቼ መብት ተጥሷል በማለት ጠቅላላ ጉባኤው እንዲታገድ ጉዳዩን ወደ መደበኛ
ፍ/ቤት መውሰዱ ተሰማ።
ነሀሴ 21 እና 22/2014 ጎንደር ላይ በሚካሄደው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለስራ አስፈጻሚነት እንጂ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም ማለቱን ማህበሩ ተቃውሞታል። ማህበሩን “ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ፍ/ብ/ችሎት ባለፈው ሀሙስ ባቀረበው የክስ ፋይል ፍ/ቤቱ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የዕጩ ፕሬዝዳንትነት መወዳደሪያ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አሊያም የዕጩ ፕሬዝዳንትነት መመዝገቢያ ቀን ማራዘሙ የፌዴሬሽኑን ቀጣይ አመት መሠረታዊ ስራዎች የሚያስተጓጉል ሆኖ የሚገኝ ከሆነ ፍ/ቤቱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በዕጩ ተወዳዳሪነትን እንዲመዘገቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እናመለክታለን” ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍ/ቤቱ አመልክተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በኢሲኤው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ “ይሄ የህግ ጉዳይ ነው መጨመርም መቀነስም አንችልም የተቀመጠውን ህግ መቀበል አለብን የተሰጣቸው መብት መከበሩ የግድ ነው” በማለት የፌዴሬሽኑ የህግ አማካሪና የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሃይሉ ሞላ ተናግረው ጉባኤው ቢያጸድቅም ወደ ስራ ሲገባ ግን ተግባራዊ ባለመደረጉ ማህበሩ ጉዳዩን ወደህግ መውሰዱ ታውቋል።
በ1994 በወጣው የዲያስፖራ አዋጅም ከሀገሪቱ የደህንነት የወታደራዊ ተቋማት አባልና መሪነት እንዲሁም የፖለቲካ አመራር ውጪ በማህበራዊ አገልግሎት ላይ እንድንሳተፍ መብት ሰጥቶን ፌዴሬሽኑ ግን ተግባራዊ አላደረገም በማለት ማህበሩ ቅሬታውን ገልጿል። ባለፉት 20 አመታት ውስጥ በተካሄዱት ምርጫዎችም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በተለይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ይህን አዋጅ ተግባራዊ እንዲደረግ አለማድረጉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን አስከፍቷል። ፌዴሬሽኑም የትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ህገመንግስታዊ መብት እንዲያከብር የእግርኳሱን ደንብ እንጂ ሀገር የሚመራበትን ህግ ማውጣት እንደማይቻል ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ አሳስበዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁትና በደንቡ ዙሪያ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ሃይሉ ሞላ በበኩላቸው ” በኢሲኤው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ ነበር እኔም የተባለውን አቋም አንጸባረኩኝ ነገር ግን ክቡር ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ደግሞ መመሪያው መከበር አለበት በማለታቸው ጉዳዩ ተንጠልጥሎ ወጣ እንጂ የጸደቀ ነገርም አልነበረም ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ደግሞ “ይህንና ሌሎች ጉዳዮች በተሰጠን አቅጣጫ መሠረት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን መተዳደሪያ ደንቡን እንጨርሳለን ብለው ወጡ እንጂ የጸደቀ ነገር አልነበረም”በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ
ፍ/ብ/ችሎት ደግሞ ጉዳዩን ለማየት ለፊታችን ማክሰኞ ሀምሌ 19/2014 ከጠዋቱ አራት ሰአት ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።