የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ይፋ ሲደረጉ በርከት ያሉ የቅጣት ውሳኔዎች ተላልፈዋል።
በተጫዋቾች ባሳለፍነው ዕሁድ ምሽት በተደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከጨዋታው በኋላ ተጫዋች በመማታት በሚል ኤፍሬም ታምራት እና በረከት ወልዴ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተበይኖባቸዋል።
ተጫዋቾቹ ከጨዋታ ቅጣቱ በተጨማሪም እያንዳንዳቸው የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
በዚህም ኤፍሬም ታምራት ክለቡ ከፋሲል ከነማ ፣ ከመቻል ፣ ከወልዋሎ አዲግራት እና ከኢትዮጵያ መድኅን የሚያደጋቸው ጨዋታዎች የሚያልፉት ሲሆን ፤ በረከት ወልዴ በበኩሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድኅን ፣ ከአርባምንጭ ከተማ ፣ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ከመቻል የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ያልፉታል።
- ማሰታውቂያ -
አንጋፋው የመቻል ተጫዋች ሽመልስ በቀለም ቡድኑ ከመቀሌ 70 እንደርታ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ላይ የጨዋታውን ዳኞች አፀያፊ ስድብ ተሳድበሀል በሚል የሶስት ጨዋታዎች እና የሶስት ሺህ ብር ቅጣት ተበይኖበታል።
በዚህም መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የማይሰለፍ ይሆናል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡናው ራምኬል ጀምስ እና የአዳማ ከተማ አድናን ረሻድ በሳምንቱ ጨዋታዎች ላይ የቀይ ካርድ መመልከታቸውን ተከትሎ ከአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ታግደዋል።