በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን መርሀግብር በዕለተ ረቡዕ ሲዳማ ቡናን ከኢትዮጵያ መድኅን አገናኝቶ በሲዳማ ቡና 1 – 0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል ።
በኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ በተመራው ጨዋታም 11 የቢጫ ካርዶች እና ሶስት የቀይ ካርዶች ሲታዩ ከኢትዮጵያ መድኅን በኩል አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ፣ ኪቲካ ጀማ እንዲሁም በሲዳማ ቡና በኩል ሙሉቀን አዲሱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናበትዋል ።
ከጨዋታው በኀላም በነበረ የአሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ አሰተያየት ወቅት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ሀይሌ ተገቢ ያልሆነ አስተያያት ሰጥተዋል ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ዳኞች እና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር በአሰልጣኙ ላይ ክስ መስርቷል ።
ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተላከው የክስ ደብዳቤም አሰልጣኝ ገብረመድህን በጨዋታው ላይ በዳኞች ሆነ ተብሎ ውጤት ማጣት እንደተፈፀመባቸው በመግለፅ በተለይም ጨዋታውን 14 ለ 11 ነው የተጫወትነው በማለት የጨዋታውን ዳኞችን ተችተዋል ብሏል ።
- ማሰታውቂያ -
ስለዚህም አሰልጣኙ በአሰተያየታቸው የዳኞችን መብት የሚፃረር ድርጊት የፈፀሙ በመሆኑ የፍትህ አካሉ ባለው የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥ ሲል ማህበሩ ጠይቋል ።