*….ዲ ኤስ ቲቪ 60 ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ
ተዋውሎ እስካሁን 148 ጨዋታዎችን አሳይቷል
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ25-28ኛ ሳምንት ድረስ የሚካሄዱ 32 ጨዋታዎች የዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት የማያገኙት የውል ስምምነቱ ስለማያስገድደው መሆኑ ተገለፀ።
የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበርና ዲኤስቲቪ መሃል ያለው የአምስት አመት ውል በየአመቱ 60 ጨዋታዎችን ብቻ በቀጥታ ስርጭት የማስተላለፍ ግዴታ የተገባበት መሆኑ ታውቋል።
60 ጨዋታዎችን የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት ተቋሙ ግን የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ 148 ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት ያስተላለፈ መሆኑ በሁለቱ ወገኖች መሃል ያለው ግንኙነት ጥሩ የሚባል እንደሆነና ተቋሙ ፕሪሚየር ሊጉን በበጎ ጎኑ እንደሚያየው በስርጭቱም ተጠቃሚ መሆኑን ያመላክታል ተብሏል። ዲ ኤስ ቲቪ ከ29-30ኛ ሳምንት የሚካሄዱ የዋንጫና ላለመውረድ የሚደረጉ ወሳኝ 16 ጨዋታዎችን ግን በቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፍ ተረጋግጧል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24 ሳምንት ፍልሚያ ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህርዳር ከተማ ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫና ለአፍሪካ ተሳትፎ የተሻለ እድል እንዳላቸው አሳይተዋል። ስድስት ሳምንት ጨዋታዎች እየቀሩ ፈረሰኞቹ በ52 ባህርዳር ከተማዎች በ50 ነጥቦች ተፋጠዋል ኢትዮጵያ መድን በ44 ፋሲል ከነማ በ37 ኢትዮጵያ ቡና በ34 ነጥቦች ከ3-5 ያለውን ስፍራ ይዘዋል።
ላለመውረድ በሚደረገው ጠንካራ ፉክክር ደግሞ 11 ነጥቦችን ይዘው በግብ እዳ ብዛት 16 ኛና 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለመውረድ የቀረቡ ሲሆን ቀሪ አንደ ወራጅ ቡድን ላለመሆን የሚጥሩት ወደ 7 የሚጠጉ ክለቦች መሃል ያለው ልዩነት ብዙም ባለመራራቁ ቀጣይ ጨዋታዎች ወሳኞች ሆነዋል።
ቀጣይ ጨዋታዎች ደግሞ የቀጥታ ስርጭት የማይኖራቸው በመሆኑ የአክሲዮን ማህበሩ የውድድርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቀሪ ጨዋታዎችን በተሻለ ትኩረት የመከታተልና የውድድሩን ተአማኒነት የማስጠበቅ ፍትህ የማስፈን ግዴታውን እንዲወጣ ተጠይቋል።