ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት መርሀግብር ብቻ የቀረው የ2015 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፕየን እና የቀጣዩ ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን በትናንትናው ዕለት አረጋግጧል ።
በተጨማሪም ባህርዳር ከተማ የ2ኛ ደረጃን በመያዝ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑ ተረጋግጧል ። በተጨማሪም ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መውረዳቸውን ሲያረጋግጡ ሶስተኛው ወራጅ ክለብ ከአርባምንጭ ከተማ እና ከወልቂጤ ከተማ አንዱ በመሆን በመጪው ሀሙስ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይታወቃል ።
ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ተጠባቂ የሆነውን የኮከብ ተጫዋች ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ ፣ ተስፈኛ ተጫዋች እና ዝርዝር ይፋ ሆኗል ።
በኮከብ ተጫዋችነት እስማኤል ኦሮ አጎሮ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ፉአድ ፈረጃ(ባህርዳር ከተማ) ፣ ያሬድ ባየህ(ባህርዳር ከተማ) ፣ ጌታነህ ከበደ(ወልቂጤ ከተማ) ፣ ባሲሩ ዑመር(ኢትዮጵያ መድኅን) ፣ አለልኝ አዘነ(ባህርዳር ከተማ) እና ቢንያም በላይ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) ተካተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በኮከብ ግብ ጠባቂ ዘርፍ ደግሞ ሶስት ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን አቡበከር ኑራ(ባህርዳር ከተማ) ፣ ፔፔ ሰይዶ(ሀዲያ ሆሳዕና) እና ቢንያም ገነቱ(ወላይታ ድቻ) ተካተዋል ።
በተስፈኛ ተጫዋቾች ዘርፍ አምስት ተጫዋቾች በዕጩነት ሲቀርቡ ዮሴፍ ታረቀኝ(አዳማ ከተማ) ፣ አማኑኤል ተርፉ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ አበባየሁ ሀጂሶ(ወላይታ ድቻ) ፣ ዘላለም አባተ(ወላይታ ድቻ) እና ፍቅሩ አለማየሁ(ለገጣፎ ለገዳዲ) ተካተዋል ።
በኮከቦቹ ምርጫ ላይ የሊጉ ተመልካቾች ድምፅ መስጠት የሚቻሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይፋዊ የቴሌግራም ገፅ ላይ ለመረጡት ዕጩ ድምፅ መስጠት ይቻላል ።
በ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጋቶች ፓኖም(ቅዱስ ጊዮርጊስ) በኮከብ ተጫዋችነት ፤ ቻርለስ ሉክዋጎ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) በኮከብ ግብ ጠባቂነት ፤ ይገዙ ቦጋለ(ሲዳማ ቡና) በኮከብ ግብ አግቢነት ፤ ተሾመ በላቸው(መቻል) በተስፈኛ ተጫዋች እንዲሁም ዘሪሁን ሸንገታ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) በኮከብ አሰልጣኝነት መመረጣቸው የሚታወስ ነው ።
በኮከብ ግብ አግቢነቱ የቅዱስ ጊዮርጊሱ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በ25 ግቦች በመምራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ጌታነህ ከበደ በ18 እንዲሁም ቢንያም ጌታቸው በ13 ግቦች የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል ።