የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እሁድ ሐምሌ 02 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ግጥሚያ(ዎችን) ጨምሮ ሌሎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ውጤት በማፅደቅ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።
በዚህም ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው አርባ ምንጭ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ በነበረው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የጨዋታ አመራሮችን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቦበታል ።
የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት ደጋፊዎቹ ተመሳሳይ ጥፋት 2 ጊዜ አጥፍተው ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አርባምንጭ ከተማ ብር 100,000/አንድ መቶ ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኖበታል ።
በተጨማሪም ሻምፕየኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ከተማ ጋር ባደረገው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የክለቡ ደጋፊዎች የተቀያሪ ተጫዋቾች መቀመጫ ጣሪያ ላይ ጉዳት ስለማድረሳቸው ሪፖርት የተደረገ በመሆኑ ክለቡ የተጎዳውን ንብረት እንዲያሰራ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የማሰሪያ ዋጋ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል ፡፡
- ማሰታውቂያ -
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎችም አምስት ተጫዋቾችና አንድ የቡድን አመራር ላይ ላይ ቅጣት ተላልፏል።
በርናንድ ኦቼንጌ(አርባምንጭ ከተማ) እና ግሩም ሃጎስ(መቻል) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ሲወሰን አህመድ ሁሴን (አርባምንጭ ከተማ) ክለቡ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የራሱን ክለብ ደጋፊዎች በምልክት አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3/ሶስት/ ጨዋታ እንዲታገድና 3000 ብር እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል።
አደም አባስ(ባህር ዳር ከተማ) ክለቡ ባደረገው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ሃይማኖታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ ስለመልበሱ ሪፖርት የተደረገበት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ተጫዋቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺህ ብር/ እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺህ ብር/ እንዲከፍሉ ፥ አቶ ጌታቸው ታዳሙ (የቡድን መሪ /ወልቂጤ ከተማ /) ክለቡ ባደረገው የ30ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ወቅት አወዳዳሪ አካልን ስለመስደባቸውና ስለመዝለፋቸው ሪፖርት የተደረገባቸው በመሆኑ የቡድን መሪው ላጠፉት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አራት/4/ ወር እንዲታገዱና የገንዘብ ቅጣት ብር 10, 000 /አስር ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡