የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ጥር 27 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች ሰባት በመሸናነፍ ቀሪ አንዱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 18 ጎሎች በ16 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 34 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ አራት ቀይ ካርድ ተመዝግቧል ።
- ማሰታውቂያ -
በሳምንቱ በሰባት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ወጋየሁ ቡርቃ(ሻሸመኔ ከተማ) ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ(ሃዋሳ ከተማ)፣ ሱሌማን ሀሚድ(ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀማቸው ቀይ ካርድ አይተው ከጨዋታ የተወገዱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ ፤ ፍሬው ጌታሁን(ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ የማግባት ዕድል በማበላሸት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል እንዲሁም ወጋየሁ ቡርቃ(ሻሸመኔ ከተማ)፣ መድሃኔ ብርሀኔ(ሃዋሳ ከተማ) ፣ አቤል አሰበ (ድሬደዋ ከተማ) እና ዳግም ንጉሴ(ሀዲያ ሆሳዕና) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ የተመለከቱ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል ።
በሶስት ክለቦች ላይም ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ(ሱሌማን ሀሚድ፣ ብሩክ እንዳለ፣ ካሌብ አማንክዋህ እና ፍሬው ጌታሁን) ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ተገኑ ተሾመ፣ ቢንያም በላይ፣ በረከት ወልዴ፣ ባህሩ ነጋሽ እና ኄኖክ አዱኛ) እንዲሁም ሃዋሳ ከተማ(አቤኔዘር ዮሐንስ፣መድሃኔ ብርሀኔ፣ እዮብ ዓለማየሁ እና አዲሱ አቱላ) በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሶስቱ ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡