ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 7ኛ ሳምንት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሁለት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሁለት ጨዋታ በአቻ ሲጠናቀቅ 9 ጎሎች በ8 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። የሳምንቱ ቀሪ አራት ጨዋታዎች በድሬደዋ አየር ንብረት የመጫወቻ ሜዳው ለማጫወት ምቹ ባለመሆኑ ላልተወሰን ጊዜ ተራዝመዋል። በሳምንቱ 24 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ ሶስት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል።
የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ህዳር 04/2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ጀማል ጣሰው(ወልቂጤ ከተማ) እና ኢዮብ ዓለማየሁ(ሃዋሳ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀማቸው ቀይ ካርድ አይተው ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ 1 ጨዋታ እንዲታገዱ እንዲሁም ፊሊፔ ኦቮኖ(ሲዳማ ቡና) ከግብ ክልል ውጭ ኳስ በእጅ በመያዝ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ 1 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
- ማሰታውቂያ -
በክለቦች ሃዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በሳምንቱ ባደረጉት ጨዋታ የክለባቸው አምስትና ከዛ በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡