የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ ሁለቱ ክልሎች በጽኑ ተቃወሙት።
የደ.ብ.ብ.ሕ.ክልል መንግስት እግርኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ ሚዛን የማይደፋ ያለውን የሊግ ኩባንያ መግለጫ ተቃውሟል።
” የአክሲዮን ማህበሩ ለሀገሪቱ እግርኳስ ዕድገትና ልማት ይሰራል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የክለቦችን አቅም ከመፍጠር አንጻር የሚጠበቅና የጀመረውን ስራ ይቀጥላል ቢባልም በማይመለከተው ጉዳይ ላይ ገብቷል” ሲል ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ” አባል ባለመሆኑ በተጋባዥነት በተገኘበት በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው 13ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ቀርቦ አስተያየት የተሰጠበትን ጉዳይ እንደ አዲስ ግኝት በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ አቅጣጫ ለማስያዝ የቀረበውን መግለጫ ሚዛን የማይደፋና እንደጠቅላላ ጉባኤ አባልነታችን አንቀበለውም” ሲል አቋሙን አሳውቋል።
የክልሉ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በሰጠው ማሳሰቢያ ” ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ለአክሲዮን ማህበሩ ከመግለጫው በፊት በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት በህግ እንዲይዘውና ውጤቱን እንዲያሳውቀን እናሳስባለን” በማለት ክልሉ የያዘውን ጠንካራ የተቃውሞ አቋም ይፋ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -
በተመሳሳይ የኦሮሚያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም አክሲዮን ማህበሩ በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊና የስራ አስፈጻሚ ምርጫን አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ የማይመለከተው ነው ሲል ኮንኗል። ፌዴሬሽኑ ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ ” አክሲዮን ማህበሩ የሰጠው መግለጫ የማይመለከተውና የስፖርት ቤተሰቡን ለማደናገርና የተዛባ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚያደርግ ነው” ብሏል።
ፌዴሬሽኑ አክሲዮን ማህበሩ ካሳየው ሀላፊነት የጎደለው ተግባሩ እንዲታቀብ ጠይቆ” ፌዴሬሽኑና የኢትዮጵያ ህዝብን በመገናኛ ብዙሀን ይቅርታ እንዲጠይቅ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑም አስተማሪ የሆነ ርምጃ መውሰድ እንዳለበት የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጽኑ ያምናል” ብሏል።
በክልል ደረጃ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል ተቃውሞ በማቅረብ ከሁሉም ክልሎች የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል።