በይደር ቆይቶ የተደረገው 46ኛው የሸገር ደርቢ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በጨዋታው ኢትዮጵያበ ቡና በኩል በረከት አማረ ፣ ራምኬል ጀምስ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ቃልአብ ፍቅሩ ፣ ሬድዋን ናስር ፣ አማኑኤል ዮሐንስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ብሩክ በየነ በመጀመሪያ አሰላለፍ ሲካተቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ባህሩ ነጋሽ ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱህ ፣ ምኞት ደበበ ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ቢንያም በላይ ፣ አቤል ያለው ፣ ቸርነት ጉግሳ እንዲሁም እስማኤል ኦሮ አጎሮ በምርጥ አስራ አንድ የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው ።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ለበርካታ ዓመታት በፕሪሚየር ሊጉ እና በአለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በዳኝነት ላገለገለችው ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊድያ ታፈሰ የሽኝት ፕሮግራም ተደርጓል ። አርቢትሯን ከሙያ ባልደረቦቿ በተጨማሪም የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በክብር ሸኝተዋታል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገበት ሆኖ አልፏል ።
በአጋማሹ በፈረሰኞቹ በኩል በተለይም ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ለረጅም ደቂቃዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው ቆይተዋል ። በተለይም የፊት መስመሩን ሲመራ ለነበረው ብሩክ በየነ በረጅም ሲላኩ የነበሩ ኳሶች በቀላሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች እግር ስር ይገቡ ነበር ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በስምንተኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን አቤል ያለው ከቢንያም በላይ የደረሰውን በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ሆኖ ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ፈረሰኞቹ ጫና ባበዙበት የቀኝ መስመር ቢንያም በላይ ይዞ የገባውን ኳሶ ለመቀነስ ያደረገው ጥረት ተቀባይ ባለማግኘቱ ሳይሳካ ቀርቷል ።
በ4 – 1 – 4 – 1 ቅርፅ ወደ ሜዳ የገባው የአሰልጣኝ ዮሴፍ ኢትዮጵያ ቡና በነዚህ ደቂቃዎች ላይ በተለይም ናትናኤል ዘለቀ ከኋላ እየተቀበለ ወደ ፊት የሚጥላቸውን ኳሶች ለመቆጣጠር ተቸግረው ቆይተዋል ።
ቡናማዎቹ ከኋላ መስርተው ይዘው የሚያወጧቸው ኳሶችም ወደ ፊት በሚደርሱበት ጊዜ ለፈረሰኞቹ ተከላካዮች ጫና የማይፈጥሩ ነበሩ ።
ለፈረሰኞቹ አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮ የሚደርሱ ኳሶችን አጥቂው ተመቻችቶ የግብ ሙከራዎችን እንዳያደርግ በማድረጉ ረገድ የቡናማዎቹ ተከላካዮች ጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽን አሳልፈዋል ።
እስከ 22ኛው ደቂቃ ድረስ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ኳስ ይዘው ለመግባት ሳይቸሉ የቆዩት ቡናማዎቹ በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ሃይለሚካኤል አደፍርስ በግራ የሳጥኑ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ለመስፍን ታፈሰ ለማቀበል ሞክሮ መስፍነ ሳይደርስበት ቀርቷል ።
መስፍን ታፈሰ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታቸው ኳሶች ኢላማቸውን መጠበቅ አልቻሉም ነበር ።
ጨዋታው 31ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቀደም ባሉት ደቂቃዎች ላይ ከነበሩት የግብ ሙከራዎች ይበልጥ ለግብ የቀረበ ጠንካራ ሙከራ ታይቷል ። ቢንያም በላይ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ያሻገረውን ኳስ አቤል ያለው በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ያደረገውን የግብ ሙከራ በረከት አማረ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በቀኝ መስመር ከአቤል ያለው ጋር በነበረው ጥምረት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲጥር የነበረው ቢንያም በላይ በአጋማሹ የመጨረሻ አንድ ሶስተኛ ደቂቃዎች ላይ በግራ መስመር በኩል ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶች አድርጓል ።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ከሳጥን በቅርብ ርቀት ሆኖ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም ያለግብ ተጠናቋል ።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በታየበት እና በሁለቱም በኩል ግቦችን የተመለከትንበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ውጤት የወሰኑ ሁነቶች አሳይቶን አልፏል ።
ቡናማዎቹ ብሩክ በየነ ወደ ኋላ በመሳብ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በሚያደርጋቸው ቅብብሎሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ መስመርን በመስበር የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶች አድርገዋል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በተለይም ከመስመር አና ከማዕዘን በሚነሱ የአየር ኳሶች ረጃጅም ተጫዎቻቸውን በመጠቀም የግብ ዕድሎች ለመፈጠር ጥረዋል ።
በ55ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መሰመር አቤል ያለው ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ናትናኤል ዘለቀ ወደ ግብ የመታውን ኳስ በረከት አማረ ግብ ከመሆን አግዶታል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው የገቡትን ኳስ በመስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ አለመግባባት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
የፈረሰኞቹ ጫና ይበልጥ አይሎ በታየባቸው ደቂቃዎች ላይ የአምና ሻምፕየኖቹ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ። ቶጎአዊው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ከጋቶች ፓኖም የተቀበለውን ኳስ በጠንካራው የግራ እግሩ አክርሮ በመምታት በ66ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
ግዙፉ አጥቂ ግቡን ማስቆጠሩን ተከትሎ በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 24 አድርሷል ።
ነገር ግን የቅዱስ ጊዮርጊሶች ደስታ መዝለቅ የቻለው ለስድስት ያህል ደቂቃዎች ነበር ። በ72ኛው ደቂቃ ላይ 10 ቁጥር ለባሹ ብሩከ በየነ ከአማኑኤል ዮሐንስ የደረሰውን አስደናቂ ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ መረብ ላይ አሳርፏል ።
በቀጣዮቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ለመውጣት ፍላጎቶች የታዩባቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻሉ ሲሆን በይበልጥ ግን ፈረሰኞቹ የተሻሉ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
በተለይም ከማዕዘን በሚነሱ ኳሶች በኦሮ አጎሮ ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱህ እና ጋቶች ፓኖም የተደረጉ ሙከራዎች ተደርገው ነበር ፤ ምንም እንኳን ኢላማቸውን መጠበቅ የቻሉ ባይሆኑም ።
የቅዱስ ጊዮርጊሱን የግብ ዘብ የፈተኑ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ያልቻሉት ቡናማዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች ስኬታማ አልነበሩም ።
በመጨረሻም ጨዋታው በአንድ ለአንድ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በ29ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 24 ቅዳሜ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡና ከመቻል እንዲሁም በተከታዩ ቀን ዕሁድ ሰኔ 25 ከ9:00 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀድያ ሆሳዕና ጨዋታውን ያደርጋል ።