*.አሰልጣኙና ፕሬዝዳንቱ ተሰናብተዋል..
ወደ ፕሪሚየር ካደጉ ሶስት ክለቦች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ መድን የክለቡን ፕሬዝዳንትና አሰልጣኝ ማሰናበቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ክለቡን ለፕሪሚየር ሊግ አብቅቶ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ይፋለማል ተብሎ ቢገመትም በሊጉ ለማለፍ የሜዳ ላይ ውጤት ብቻ አይደለም ብዙ ሸፍጦችና የኳሱ ፖለቲካ ማወቅን ይጠይቃል የሚል ዕሳቤ ባላቸው አመራሮች ተሰናብቶ የቅጥር ውሉ ይፋ ባይደረግም በቅርቡ በሲዳማ ቡና አመራሮቸ የተባረሩት አሰልጣኝ
ገ/መድህን ሃይሌ መቀጠራቸው ታውቋል።
የክለቡ ስራ አስፈጻሚ አባላት አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ያለውን የትምህርት ዝግጅትና ውጤታማነትን ከግምት አስገብተውና መርጠው ቢልኩም የበላይ አመራሮቹ ብቻውን ሳይሆን ልምድ ካላቸው አሰልጣኞች ጋር አወዳድራችሁ ላኩ በመባላቸው የስራ አስፈጻሚ አባላቱ እንደገና አወዳድረው ከዲሲፕሊንና አቅም ጋር ክለቡን በጸሎት ቡድኑንና ተጨዋቾቹን እንደማወቁ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል በምንፈልገው መንገድ ይጓዛል በሚል ድጋሚ ቢመርጡም የሁለቱ ወሳኝ አመራሮችን እምነት ሳያገኝ ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
ክለቡን ለረጅም አመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ተምትም ሁለት አመት አብረው እንደሰሩ አመራር በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑል ሰገድ ላይ በያዙት ጠንካራ አቋም ይመስላል የስንብት ደብዳቤ ደርሷቸዋል። ፕሬዝዳንቱና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በያዙት አቋም የተበሳጩት ከፍተኛ አመራሮች አዲስ ኮሚቴ አዋቅረው አሰልጣኙ ገ/መድህን ሃይሌ መሆኑን ገልጸው ወደ ስራ መግባታቸው ታውቋል።
ክለቡ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ አቶ ተምትምን ያሰናበተበት ደብዳቤ ግን ግርምት የሚፈጥር ሲሆን ” …..ለረጅም ጊዜያት ክለቡን በማገልገልዎ ዕረፍት እንዲወስዱ ታስቦ….” የምትለዋ ሀሳብ ፕሬዝዳንቱ በአሰልጣኝ በጸሎት ላይ በያዙት አቋም አመራሮቹ መከፋታቸውና ስንብቱ የዚህ ውጤት ነው እንዳይባል አቅጣጫ ለማስቀየስ የተጠቀሙበት መሆኑ የብዙዎች ግምት ሆኗል።
ሁለት ተከታታይ አመታት ከጅማ አባጅፋርና ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ብቸኛው አሰልጣኝ የሆኑት አሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌ መድንን የት ድረስ ያደርሱት ይሆን? የሚለው ግን ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።