” ምንም መልካም ነገር ብንሰራ ሌቦች መባላችን አይቀርም በኛ በኩል ግን ህግን ተከትለን የደጋፊዎቻችንን ክብር ለመጠበቅ ጥረት አድርገናል”
አቶ ገዛኧኝ ወልዴ
/ የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራ አስኪያጅ/
**…. ከነገ ጀምሮ ሽያጩ ይካሄዳል
**…..ዋጋው 800 ብር ነው ተብሏል
በየአመቱ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ “ቡንዬ የኔ” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ግንቦት 11/2016 መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ይካሄዳል።
- ማሰታውቂያ -
በእስካሁኖቹ ስድሰት ቤተሰባዊ ሩጫ ላይ አምስቱ በጎዳና ላይ ሲካሄዱ አንዱ በኮቪድ 19 ምክንያት 30 ሺህ የክለቡ ደጋፊዎች ማሊያ ገዝተው ባሉበት የበጎ አድራጎት ስራ ላይ በመሳተፍ ቀኑን ማሳለፋቸውን የክለቡና የደጋፊ ማህበሩ አመራሮች በሰጡት መግለጫ ላይ አስረድተዋል።
ዛሬ ከቀትር በኋላ በካሌብ ሆቴል በተሰጠ መግለጫ ላይ የሩጫ ውድድሩ በቀጣዩ ግንቦት 11/2016 የሚካሄድ ሲሆን የቲሸርቱ ዋጋ 800 ብር መሆኑና ከነገ ጀምሮ ሽያጩ በቡና ባንክ ሙሉ ቅርንጫፎች፣ በክለቡና በደጋፊ ማህበሩ ጽ/ቤቶች ፣ በክለቡ ስር በታቀፉ 13 ዕድሮችና ክለቡ በመረጣቸው ደጋፊዎች እንደሚከናወን አስረድተው በሚገዙበት ጊዜ ደረሰኙን በትክክል እንዲይዙና ማሊያውን ከወሰዱበት ቦታ ብቻ እንደሚያገኙ አሳስበዋል።
“የቤተሰባዊ ሩጫው ዋና አላማ ክለቡን በገቢ ማጠናከርና የደጋፊውን ቤተሰባዊ ትስስር የተሻለ ማድረግ ነው። ማሊያው የሩጫ ነው የክት እንደምንለው አይደለም አላማው ገንዘብ ማሰባሰብ መሆኑን መታወቅ አለበት በሩጫውም 35 ሺህ ሰው ይገኛል ብለን እንጠብቃለን”
ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ገዛኧኝ ወልዴ እንደገለጹት ” ምንም መልካም ነገር ብንሰራ ሌቦች መባላችን አይቀርም በኛ በኩል ግን ህግን ተከትለን የደጋፊዎቻችንን ክብር ለመጠበቅ ጥረት አድርገናል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ ገዛኧኝ ክለባችን ከሌሎች ክለቦች የሚለየው የፋይናንስ ምንጩ ህዝቡ መሆኑ ነው ለዚህ ነው ክለቡ ህዝባዊ ነው የምንለው ” ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።
የደጋፊ ማህበሩ አመራር የሆኑት አቶ ሰለሞን ታምራት
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የሩጫ ውድድሩን በደንብ ጓጉቶ እንደሚጠብቀው አውቃለሁ ደጋፊያችን ማን እንደሆነ የሚያሳይበት ውድድር በመሆኑ የተነሳንበት አላማ እንደሚሳካ እምነቱ አለኝ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ኬ ሀውሲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሩጫ ውድድሩ የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር መሆኑም ይፋ ተደርጓል። የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ “የዚህን ተወዳጅና የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆነውን ኢትዮጵያ ቡናን ስፖንሰር በመሆናችን ትልቅ ኩራት ተሰምቶናል ድርጅታችን በ10 አመት ውስጥ 100ሺህ ኢትዮጵያዊያንን የቤት ባለቤት ለማድረግ አቅዶ የተመሰረተ ነው በዚህ ሰአት የመጀመሪያው ዙር ቤት ለደረሳቸው እድለኞች ርክክብ እያደረግን ነው አዋጭና አስተማማኝ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ያለው ስራ እንሰራለን ብለን እናምናለን ለውድድሩም ስኬት መልካም እድል እንላለን” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዚህ የክለቡ የቤተሰባዊ የሩጫ ውድድር ላይ ከኬ ሀውሲንግ ውጪ ሀበሻ ቢራ፣ ቡና ባንክ፣ ቤቲካ፣ና ከሀ እስከ ፐ የተሰኙት ተቋማትም በአጋርነት ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለጽ አመራሮቹ አመስግነዋል።