” ዋንጫ ማምጣት እንደምችል አምናለሁ ” አሰልጣኝ ተመስገን ዳና
” ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ለማምጣት በሂደት ላይ ነን ” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በዛሬው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታድየም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ፤ የአሰልጣኞች ስታፍ ፤ ከክለቡ ጋር የሚቀጥሉ ተጫዋቾች እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾችን ከደጋፊው ጋር የማስተዋወቅ ስነ ስርዓት አካሂዷል ።
የስፖርት ክለቡን በፋይናንስ ከማጠናከር ጋር በተያያዝ በተከታታይ ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ ያለው እና ከሳምንት በፊት የብራንድ ሾፑን በይፋ የከፈተው ክለቡ የገቢ ማሰባሰቢያው አንድ አካል የሆነውን እና አዳዲስ ተጫዋቾችን ለደጋፊው የማስተዋወቅ መርሀ ግብር ነው በዛሬው ዕለት ያደረገው ።በመርሀ ግብሩ ማስጀመርያ ላይ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የክለቡን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ንግግር አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
” በ2015 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከነበሩት ተጫዋቾች በአሰልጣኙ ፍላጎት መቅረት የሚገባቸው በዲሲፕሊናቸው በብቃታተቸው ተመዝነው ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ተጫዋቾች ብቻ እንዲቀሩና የዋና ቡድኑ አካል እንዲሆኑ ተደርጓል ። ”
” ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ወደ ስደስት ተጫዋቾች ዋናውን ቡድን ተቀላቅለው የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅት እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል ። አሰልጣኙም ከነሱ አይቶ የሚወስዳቸው ተጫዋቾች ይኖራሉ ።” በቡድናችን ውስጥ አሁንም የጎደሉ ተጫዋቾች አሉ ። የጎደለ ዲፓርትመንተ አለ ። ከአሰልጣኙ ጋር ተነጋግረን ከዚህ በፊት እንደነበረው ዝም ብሎ ተጫዋች እያግበሰበሱ መሞከር ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚጫወቱ ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ለማምጣት በሂደት ላይ ነን በሚቀጥለው ሳምንት እናጠናቅቃለን ብለን እናስባለን ። ”
” በለንድን የሚኖር ትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ የአካል ብቃት አሰልጣኝ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት ተጫዋቾቻችን የአካል ብቃት ስልጠና እንዲወስዱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ትኬት ተልኮለታል ። ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከኛ ጋር በመቀላቀል ስራውን ይሰራል ። ”
” ነባርም ሆነ አዳዲስ ተጫዋቾች ከናንት የሚጠበቀውን አድርጉ ከኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ዝግጁ ነን ። በመጀመሪያው ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ስንጫወት ፊት ለፊታችን ዋንጫ ተቀምጦ ነው የምንጫወተው ። በእያንዳንዱ ጨዋታ ደጋፊው መስዋዕትነት እንድትከፍሉ ይፈልጋል ። መስዋዕትነት ከፍላቹ ብትሸነፉ ደጋፊው ያጨበጭብላችኋል ። “ዋና አሰልጣኙ ተመስገን ዳናም በመድረኩ ላይ ተከታዩን ንግግር አድርጓል ።
” ማሰልጠን ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ቀን እንደማሰለጥን በቅርቤ ላሉ ሰዎች እናገራለሁ ። ዛሬ ያንን አሳክቻለሁ ። ”
” የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ መሆን ብቻ ለኔ ስኬት አይደለም ። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ዋንጫ ማንሳት እፈልጋለሁ ። “” እኔ ዋንጫ ማምጣት እንደምችል አምናለሁ ”
የክለቡ ነባር ፤ አዳዲስ እና ከ20 ዓመት በታች ያደጉት ተጫዋቾች በደጋፊው ፊት ኳስ የማንጠባጠብ እና የፎቶ ፕሮግራም ካደረጉ በኋላ መርሀ ግብሩ ተጠናቋል ።
ክለቡ የቅድመ ወድድር ዝግጅቱን በነገው ዕለት ወደ ሀዋሳ በማቅናት የሚያደርግ ይሆናል ።