ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ መለያየቱን ተከትሎ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከስንብት ተርፏል።
በሁለቱ ወገኖች ውል መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከተሸነፈ አሰልጣኙ ይሰናበታል በሚል የተቀመጠው ውል ሶስተኛውን ጨዋታ በአቻ ውጤት በማጠናቀቁ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል። መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ዘንድሮ ዋንጫ ካጣን አሊያም በሶስት ተከታታይ ጨዋታ ከተሸነፈ በውሉ መሠረት ይሰናበታል ሲሉ በቅርቡ ሊሆን የሚችለውን አሳውቀዋል።
በሁለቱ የደቡብ ክለቦች ሀድያ ሆሳዕናና በሀዋሳ ከተማ የተሸነፉት ቡናማዎቹ ሶስተኛ ሽንፈት ሳይገጥማቸው አቻ ወጥተዋል። በመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የሚመራው የኢትዮጵያ ቡና ቦርድ ከዳዊት እስጢፋኖስና ከአሰልጣኝ ዘላለም ጸጋዬ ተቃራኒ በመቆም አሰልጣኙ እየፈለጋቸውም ቢሆን ዳዊት የክለቡን ማሊያ አይለብስም አሰልጣኙ ዘላለም ደግሞ ውሉ አይታደስለትም በሚል አቋም መጽናቱ የሚታወቅ ሲሆን አሰልጣኝ ካሳዬ በዘላለም ምትክ እስካሁንም ድረስ ተተኪ ረዳት አሰልጣኝ አለማምጣቱ በክለቡ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆኑን ያሳየ ሆኗል።
ከሰሞኑ የአጥቂው አቡበከር ናስር የደቡብ አፍሪካ ጉዞ ጋር ተያይዞ ከአሰልጣኙና ከክለቡ አመራሮች የወጡት መረጃዎች መለያየት በውስጣቸው ያለውን መጓተት አመላካች ሆኗል። አሰልጣኝ ካሳዬ በአብዛኛው በሚዲያ መቅረብ ላይ ፍላጎት ባይኖረውም ትላንት ከአዳማ ጨዋታ በኋላ ለሱፐር ስፖርት የሰጠው አስተያየት ሲታይ ሙሉ ያለውን የእስካሁኑን ሁኔታ የሚገልጽ መግለጫ ቢሰጥ ሌላ ውዝግብ የሚነሳባቸው ጉዳዮች እንዳይኖር ተስግቷል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ካሳዬ” በኔ በኩል ስለ አቡበከር ናስር ቀጣይ ሂደት የማውቀው ነገር የለም በቀጣይ ጨዋታ ልጠቀምበት አልጠቀምበት ከጽ/ቤቱ የደረሰኝ መረጃ የለም ሁኔታውን እንደማንኛውም ሰው በማህበራዊ ሚዲያ ነው የሰማሁት” ሲል ለሱፐር ስፖርት የሰጠው አስተያየት ክለቡ እያገዘው አይደለም የሚል ትችት እያሰነዘረ ነው።
ክለቡ ግን ” ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ጥያቄው የመጣው ቅዳሜ ሆኖ ካሳዬ ሰኞ ጠዋት ስለቡድኑ ጉዞና ቀጣይ ዕቅድ ልንነጋገር ቢሮ ሲመጣ ስለሂደቱ ነግረነዋል አስቀድሞም ከቡድን መሪው ሰምቷል አያውቅም የሚለው ስህተት ነው በወቅቱ ተጨዋቹ ቪዛ ካላገኘ ነገውኑ ቡድኑን ይቀላቀል ብሎ ነግሮን ሄዶ አላወቀውም ማለት ተገቢ አይደለም አቡበከር ቪዛውን ለመቀበል ኤምባሲ ሲገባና ተሳክቶለት ቪዛውን ሲወስድ ግን አልነገረንም መሳካቱን ያወቅነው ክለቡ ከደቡብአፍሪካ መረጃውን ሲሰጠን ነው ተጨዋቹ ለካሳዬ የነገረውም ነገር የለም” በማለት ከሳምንት በፊት ምላሹን ሰጥቷል።
የክለቡ አመራሮች “ካሳዬን ጠይቁት አይዋሽም” በማለት ደጋግመው የሚመሰክሩለት ካሳዬ አራጌ የተናገረው እውነት ከሆነ የክለቡ አመራሮች ድርጊት ለክለቡ ብራንድና ታሪክ የማይጨነቁ መሆናቸውን ያሳያል በማለት ደጋፊዎቹ እየተቃወሙት ነው። በሰለጠነው አለም የክለቡ አሰልጣኝ ውሳኔ ሳይጠየቅ ምንም ውሳኔ የማይወስኑ የክለብ አመራሮችን እያየን በኢትዮጵያ ቡና ግን እንኳን ሀሳቡ ሊጠየቅ ከአሰልጣኙ በተቃራኒው ቆመው ከተጋጣሚ ክለቦች በላይ ቦርዱ የካሳዬ ከባድ ተፋላሚ ሆኗል በሚል ቦርዱና ስራ አስኪያጁ ላይ ጣት የሚቀስሩ የክለቡ ደጋፊዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ኢትዮጵያ ቡና በ12ኛው ሳምንት መርሃግብር የፊታችን ሃሙስ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የሚጫወት ይሆናል።