ከወትሮው በተለየ መልኩ ክለቦች ከመንግስት ጥገኝነት ተላቀዉ ራሳቸዉን ለመቻል በሚመስል መልኩ የተለያዩ ስፖንሰሮችን ለማግኘት በሚታትሩበት በዚህ ወቅት የመዲናዋ ክለብ የሆነዉ ኢትዮጵያ ቡና ተጨማሪ ሌላ ስፖንሰር ማግኘቱ ተሰምቷል።
በተለይ ከተለያዩ ስፖንሰሮች ጋር በአጋርነት በመስራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣዩ ሳምንት ረብዑ ደግሞ ስድስተኛ ስፖንሰሩ ከሚሆነው የራይድ ትራንስፖርት ጋር ረፋድ 3:30 ሰዓት ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ስምምነቱን የሚፈፅም ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም በዕለተ ማክሰኞ ኢትዮጵያ ቡና ከነባር አጋሩ ከሀ እስከ ፖ ጋር አስቀድሞ ባለዉ ዉል መሰረት የተዘጋጁለትን አዳዲስ ማልያዎቸን እንደሚያስተዋዉቁ ተገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ እስከዛሬ ከተለያዩ ስፖንሰሮች ጋር በመስራት ላይ ካሉት ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ከመሳሰሉት ቡድኖች በተጨማሪም ከቀናት በፊት አዳማ ከተማ ከዋሊን ቢራ ጋር ወደ ስልሳ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ እና የአይነት ገቢ የማያስገኝለት የአምስት አመት ስምምነት መፈፀሙ ይታወቃል።