በቅድመ ዉድድር ዝግጅት ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ረፋድ 4:00 ሰዓት ላይ የወዳጅነት ጨዋታቸውን ቢሾፍቱ ላይ አድርገዋል።
ከሁሉም ክለቦች አስቀድሞ ዝግጅቱን በቢሾፍቱ የጀመረዉ እና በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆነዉ የካሳየ አራጌ ስብስብ በዛሬው ዕለት ከሌላኛው የመዲናዉ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገዉ የአቋም መለኪያ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 በሆነ ዉጤት ተሸንፏል።
በዛሬዉ ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች በኩል ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾቻቸውን ለብሔራዊ ቡድን በማስመረጣቸዉ ምክንያት በአብዛኛዉ በክረምቱ የተጨዋቾች የዝዉዉር መስኮት ክለቦቹን የተቀላቀሉ እንዲሁም በቅድመ ዉድድር ዝግጅቱ ላይ እየተተሳተፉ የሚገኙ ተጫዋቾችን አስለፈዉ ለመጫወት ችለዋል።
የሀገሪቱ የከፍተኛ ሊግ እርከን (ፕሪሚየር ሊግ) ክለቦች ለ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ዉድድር ለመዘጋጀት የቅድመ ዉድድር ዝግጅታቸውን እንደጀመሩ ይታወቃል።