*…የቦርድ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔ እየተተገበረ ነው….
*….የቀጣዩ አሰልጣኝ ማንነት በምስጢር ተይዟል….
*…ፌዴሬሽኑ በዝውውር ህግና ደንብ ዙሪያ ስልጠናም
እየሰጠ ነው….
የኢትዮጵያ ቡና የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ ኢትዮጵያ ቡና ሻምፒዮን ለመሆን አቅም በሚኖረው መልኩ ራሱን እንደሚያጠናክር የገቡት ቃል መተግበር ጀምሯል።
በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ42 ነጥብና 8 የግብ ዕዳ 6ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ከያዛቸው ተጨዋቾች መሃል በእስካሁኑ አምበሉ አማኑኤል ዮሀንስ፣ ተከላካዩ አስራት ቱንጆ፣ ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች በረከት አማረና እስራኤል መስፍን.፣ ታዳጊዎቹ ገዛኸኝና ሱራፌል ጨምሮ ከ10 የማይበልጡ ተጨዋቾች ብቻ ሲቀሩ ቀሪዎቹ ውል ያላቸው በስምምነት ውላቸው ያለቀ ደግሞ ውላቸው ሳይታደስ ቡድኑን እንዲለቁ የሚደረግ መሆኑ ከክለቡ ተጨዋቾች የተገኘ መረጃ ያስረዳል። ክለቡ ውል ያላቸውን ተጨዋቾች በስምምነት እንዲለያዩ መጠየቅ መጀመሩም ታውቋል።
እስካሁን ባለው መረጃ በዲሲፕሊን ደመወዙን ከተቀጣው ዊሊያም ሰለሞን፣ ከሶስት ወር የደመወዝ ቅጣት በኋላ የመጀመሪያ ደመወዙን የወሰደው ታፈሰ ሰለሞንና ሚኪያስ መኮንን ጨምሮ አብዛኞቹ ቡድኑን እንደሚለቁ እየተገለጸ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ከአቡበከር ናስር ዝውውር የተገኘውን ገንዘብ ለዘንድሮ ዝውውር እንዲውል መወሰኑም እየተነገረ ነው።
- ማሰታውቂያ -
መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ ቡድኑ የአዳማውን ውድድር ተጠናቆ ባህርዳር ከተማ በገባበት ጊዜ ” ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ ደካማ የሆነ ውጤት እንዳይመዘገብ የምትችሉትን ጣሩ በቀጣይ የውድድር አመት ግን ውጤታማ አሰልጣኝና ለዋንጫ የሚፋለም ስብስብ ይኖረናል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን የመቶ አለቃ ፈቃደ ንግግር በቀጣዩ አመት ሊመጣ የሚችለውን አሰልጣኝ ባያሳውቅም ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ግን እንደማይቀጥሉ ያመላከተ ሆኗል። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰአት ድረስ ቡናማዎቹ መስፍን ታፈሰን ከሀዋሳ ከተማ፣ መሀመድ ኑርን ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁን ከወልቂጤ ከተማ፣
ሃ/ሚካኤል አደፍርስና ዱሬሳ ዱቢሻን ከሰበታ ከተማ ለማስፈረም መስማማታቸው ከታማኝ ምንጭ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ነገ ዓርብ ሀምሌ1/2014 በይፋ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
ፌዴሬሽኑ ከሀምሌ አንድ በፊት ለፕሪሚየር ሊጉ ወንድና ሴት ተጨዋቾች የዝውውር ህግና ደንብ ዙሪያ በዳይሬክቶሬቱ ሃላፊ ወ/ሮ ዘውድነሽ ይርዳው አማካኝነት በጁፒተር ሆቴል ስልጠና መስጠት ጀምሯል።