የኢትዮጵያ መድን ስፖርት ማህበር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በክለቡ ስር ያሉ ስፖርተኞች ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ እንዳይሰጡ ማገዱን አስታወቀ።
የክለቡ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቀምጦታል በተባለው አቅጣጫ የእግርኳስ ቡድኑ አባላት ምንም አይነት ጋዜጣዊ መግለጫም ሆነ ቃለምልልስ እንዳይሰጡ መወሰኑ ተቃውሞ ገጥሞታል። ውሳኔው የታወቀው ተጨዋቾችን ቃለምልልስ ለመስራት ሙከራ ባደረግንበት ጊዜ ሲሆን የክለቡ ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን አንበሴ ” ከበላይ አለቆች በተሰጠ መመሪያ መሰረት የእግርኳስ ቡድኑ አባላት ክለቡን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫም ሆነ ቃለምልልስ መስጠት አይችሉም ይሄን ትዕዛዝ እናከብራለን ” ሲል የክለቡን ጠንካራ አቋም አሳውቋል። የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው ቡዛየሁ በበኩላቸው ” ክለባችን ከ17 እና 20 አመት በታች እንዲሁም ዋና ቡድን ይዟል። እነዚህ የቡድኑ አባላት ክለቡን በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ ለሚዲያ እንዳይሰጡ ታዟል። እኛም የክለቡ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰጠውን አቅጣጫ እናከብራለን ተፈጻሚነቱንም እንከታተላለን ከዚህ የተለየ የምለው ነገር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከ16ቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለሚዲያ መግለጫ
አትስጡ ያለው ኢትዮጵያ መድን ብቻ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በቡድን መሪው አዳነ ግርማ ዕውቅና የሚፈለጉት ተጨዋቾች መግለጫ የመስጠት መብታቸው እየተከበረ ይገኛል። 14ቱ ክለቦች ግን ተጨዋቾቻቸውን ቃለምልልስ የመስጠት መብትና የመገናኛ ብዙሃኑም መረጃ የማግኘት መብት አክብረው እየሰሩ ይገኛል።
ኢትዮጵያ መድን ዲኤስ ቲቪ ላይ አሰልጣኙ ገብረመድን ሃይሌ ከሚፈለገውና ከተመረጠው ተጨዋቾች ጋር በጋራ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን ክለቡ ሌሎችን ሚዲያዎች ያገደው እንደ ዲ.ኤስ.ቲቪ በውል ላይ የተመሰረተ የጥቅም ግንኙነት ስለሌላቸው ነው እንዴ..? ሲል የስፖርት ቤተሰቡ ውሳኔውን ተችቷል።
- ማሰታውቂያ -
የ14ቱን ክለቦች ነጻነት ያደነቀውና ወጥ በሆነ አካሄድ በክለቡ ዕውቅና ተጨዋቾቹ የሚሰጡትን ቃለምልልስ የፈቀደውን የቅዱስ ጊዮርጊስን አካሄድ ያሞገሰው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ባለሙያ ግን “የኢትዮጵያ መድንን ዕገዳ መብት የመርገጥ ያህል ነው” ሲል ተቃውሞታል።
ክለቡ በዋነኛው የዋንጫ ተፎካካሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ1 ተረትቶ በአንጻሩ ደግሞ 3ኛ የነበረው ባህርዳር ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3 ለ 1 ማሸነፉን ተከትሎ መድንን በግብ በልጦ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ መድኖች ወደ 3ኛ ደረጃ ዝቅ ብለዋል። ኢትዮጵያ መድን የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 10 ሰአት በ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃግብር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።