በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚታየው የዳኞች ስህተት ከብቃት ይልቅ ኮታን መሰረት ያደረገ ምደባና እድገት በመኖሩ ነው የሚሉ ቅሬታዎች እየተደመጡ ነው፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያለፈለጉ ነገር አርቢትር ለሀትሪክ እንደገለፁት “በኮታ የሚደረግ ምርጫና ምደባ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥርና ግጥሚያዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ውሣኔ እንዲወሰን የሚያደርግ ነው ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴም ይህን አውቆ ማስተካከያ መውሰድ አለበት” ብሏል፡፡ በአቶ ኢብራሂም መሐመድ የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ዳኞችን አሳድጓል፡፡ ከብሔራዊ ሊግ 14 ዋናና 20 ረዳት ዳኞችን ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያሳድግ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ በተመሳሳይ 14 ዋናና 20 ረዳት ዳኞችን አሳድጓል፡፡ ተቃውሞ እየነሳበት ያለው ደግሞ የእድገቱ አካሄድ ኮታ ላይ ያመዘነ ነው መባሉ ነው፡፡
ልምድ ካላቸው ረዳት ዳኞች መሃል ለሀትሪክ አስተያየቱን የሰጠው ረዳት ዳኛ “ እድገቱ ተገቢነት ያለው መሆኑን አልክድም መሆንም ነበረበት ነገር ግን ያደጉት ሲታዩ በአቅም ብቻ መሆን ሲኖርበት በኮታ መደረጉ ትልቅ ስህተት ነው አለም ሁሉ የሚያው ጨዋታ ላይ ፕሪሚየር ሊጉን የሚመጥን ዳኝነት መታየት የግድ ይላል እየሆነ ያለው ግን ይሄ አይደለም በአዲስ አበባው ጨዋታ ብቻ ወደ 5 የሚጠጉ ውጤቶች በዳኝነት ስህተት ተቀይረዋል፤ በጅማው ሁለት ጊዜ ገጠመኙን አይተናል ይሄ አሁንም ቀጣይነቱ አያጠያይቅም፤ ዳኝነት በብቃት እንጂ በኮታ መሆን አልነበረበትም” በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡
የዋሊያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተም “በዲ.ኤስ.ቲቪ መታየቱ አጋነነው እንጂ ስህተቱ በፊትም የነበረ ነው፡፡ የቪዲዮ መረጃ ይዤ ለትምህርት እንዲሆን ለዳኞቹ ያሳየሁበት ጊዜም አለ፡፡ አሁን ስጋቴ ዳኞቹ ጫና ላይ በመሆናቸው ኦፍሳይድ የሆነ ኳስ ለቀው ግብ ገባ ተብሎ ሲተቹ በጫና ንፁህ ግብ እንዳይሽሩም እሰጋለሁ ከጫና ተላቀው በተቻለ አቅም ግጥሚያዎችን ቢመሩ የተሻለ ይሆናል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
“ግጥሚያውም በዲ.ኤስ.ቲቨ መታየታቸውን ተከትሎ ከጨዋታዎቹ ብቃት ይልቅ የዳኝነት ስህተቱ ሊጉን የሚያሳይ እንዳይሆን ያሰጋኛል፡፡ ሰበታ ከተማ ላይ ሁለት ጊዜ የደረሰው ውጤት ቅልበሳ ቅር የሚያሰኝ ነው ቀጣይ እንዳይሆን በተለይ ረዳት ዳኞች ሊበረቱ ይገባል ሲል” ልምድ ያለው ዳኛ ተናግሯል፤ የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ “ሁለት ጊዜ የደረሰብን የዳኝነት ስህተት ቅር አሰኝቶኛል፡፡ አውቀው ነው ያደረጉት የሚል እምነት የለኝም እኛም እንደምንሳሳተው እነርሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ ዳኞቹ የጨዋታው ህይወት መሆናቸውን ተረድተው በየግጥሚያው ዝግጁ ሆነው በጥሩ ሁኔታ በመዳኘት ውጤት ለዋጭ ከሆነ ስህተት እንደሚታረሙ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል፡፡
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ የፕሪሚየር ሊጉን ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ምደባ ማካሄድ የለበትም ኢንተርናሽናል ዳኞችን በብዛት ሊመድብ ይገባል፤ አለም የሚያየው ግጥሚያ እንደመሆኑ ሊጉን የዳኞች መሞከሪያ ከማድረግ ሊታቀብ ይገባል የሚል አስተያየትም እየተደመጠ ነው፡፡ ጅማ እየተደረገ ላለው ጨዋታ 26 ዋናና ረዳት ዳኞች የተጓዙ ሲሆን ከ13 ዋና ዳኞች ኢንተርናሽናሎቹ ብሩክ የማነብርሃንና ኃይለ ኢየሱስ ባዘዘው ከ13ቱ ረዳት ዳኞች ደግሞ ኢንተርናሽናሎች ትግል ግዛውና ሸዋንግዛው ተባበል ብቻ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሌሎቹ ፌዴራል ዳኞችና አሁን ካደጉ መሀል መገኘታው ምደባው ላይ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ በምደባው የተከፋ አንድ ረዳት ዳኛ ለሀትሪክ “ችግሩን እንዲፈታ የዳኞች ዲፓርትመንት የሚሰራው ስራ ሁሉን አቀፍና ወቅታዊ አቋም ላይ ያነጣጠረ እንጂ ስምና እውቅናን ብቻ ማየቱን ማቆም አለበት፤ ኮሚቴው አካባቢን ያለማከለ ሥራ ይስራ እንጂ ችሎታ ሞልቶ የተረፋቸው ግን ተስፋ ያልቆረጡ ዳኞቻችንን መፈለግ የግድ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡
በቀረቡት የምደባ ችግሮችና ቅሬታዎች ዙሪያ የተጠየቁት የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መኮንን አስረስ በበኩላቸው “ኮታ የሚባል ነገር የለም ይሄ ትክክለኛ መረጃ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክትል ሰብሳቢው ለሀትሪክ ሲናገሩ “ምርጫው ምንም አይነት አጀንዳ የለውም ኮታ የሚባልም ነገር የለም፡፡ 2012 በኮቪድ19 ምክንያት በመቆሙ ምንም ውድድር የለም በሚለው ያጫወቱበትንም ከግምት አላስገባንም፡፡ መነሻ ያደረግነው የ2011 ውድድር፣ የፋይል ጥራት፣ የመሩትን ቶርናመንትና የወደፊቱ ተስፋ ምንድነው በሚል ገምግመን ነው ወደ ምደባው የገባነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ መኮንን ሲቀጥሉ “ግድፈት ያለበትን ሰርዘን ኮከብ የተባሉ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ዳኞችን መርጠናል፤ በ2011 አንዳንዱ ዳኛ 3 ሌላው ደግሞ 10 ጨዋታ መርቷል፤ በኛ በኩል የጨዋታ ብዛትን አይተን በትንሹ 5 ጨዋታ ያጫውቱንና ከዚያ ላይ የመሩትን ጥሩ የተባሉ ዳኞችን መርጠን በአጠቃላይ ድምር ውጤት ልንለይ ችለናል ከዚያ ውጪ ኮታ የሚባል ነገ የለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ዳኞች እንጂ የወረዱ ዳኞች የሉም ይሄስ ለምን ሆነ የተባሉት አቶ መኮንን “የሚወርዱ ዳኞችን በተመለከተ ኮሚቴው ተነጋግሮበት ወደ ተግባር መግባታችን የግድ ነው፤ በፊፋ ሕግ የሚደግፈንን አላገኘንም እንጂ ኮሚሽነሮችንም እናወርዳለን፤ አይናቸው የሚያዩና መራመድ የማይችሉ ኮሚሽነሮችን እናወርዳለን፤ አሁን በቶርናመንቱ ምክንያት ከአዲስ አበባ ስላወጣን እንጂ ይሄኔ የወራጅ ዳኞችን ዝርዝር ሰርተን እንጨርስ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ በፍፁም ኮታ የሚል ነገር የለም ይህንንም አንቀበልም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ትናንት ከቀትር በኋላ በተደመጠ ዜና የሰበታ ከተማና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ላይ የዳኝነት ስህተት ፈፅመዋል የተባሉትን ፌዴራል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሰና ፌዴራል ረዳት ዳኛ ባደታ ገብሬን ለስድስት ወር ምንም አይነት ጨዋታ እንዳይመሩ መታገዳቸው ታውቋል፡፡