የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በቀድሞ አሰልጣኙ ሃይሉ ነጋሽ/ቲጋና/ ክስ ዙሪያ በዲሲፕሊን ኮሚቴ የተሰጠውን ብይን በመቃወም ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ።
የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከተመለከተ በኋላ በሰጠው ውሳኔ “ክለቡ ቀሪ የአሰልጣኙን ደመወዝ እንዲከፍል አሰልጣኙን ወደስራ ገበታቸው እንዲመልስ ይህ የማይሆን ከሆነ እስከ ውላቸው የመጨረሻ ቀን ድረስ ያለውን ደመወዛቸውን እንዲከፍል ውሳኔውንም በ7 ቀን ውስጥ እንዲፈፅም” ሲል የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ፋሲል ከነማ ይግባኝ ቢልም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ግን የዲሲፕሊን ኮሚቴን ውሳኔ አጽንቷል።
የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከክለቡ የቀረበውን ቅሬታና የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔን ከመረመረ በኋላ በ1/10/2015 ይፋ በተደረገው ውሳኔ ክለቡም አሰልጣኙን ሲያሰናብት በዲሲፕሊን መመሪያው አንቀጽ 80/26 በቂ ጊዜ ስለመስጠቱ ስንብቱም በውል ስምምነታቸው መሰረት ስለመካሄዱ ማጣራቱን ገልጿል።
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው እንዳስረዳው ተሻሽሎ በቀረበው የዲሲፕሊን መመሪያ አንቀጽ 90 ተራ ቁጥር 2 መሰረት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ የፍሬ ነገርም ሆነ የህግ ስህተት የሌለበት ነው በማለት ” የዲሲፕሊን ኮሚቴ በፋሲል ከነማ ላይ የሰጠው ውሳኔ እንዲጸናና ክለቡም ለይግባኙ ያስያዘው ገንዘብ ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲደረግ ተወስኗል” ሲል ብይኑን ሰጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱ የፍትህ አካላት ውሳኔ መሰረት ክለቡ የአሰልጣኙን ቀሪ የ6 ወር ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ውስጥ የገባ ሲሆን በጸናው ውሳኔ መሰረት ተግባራዊ ካላደረገ ከክረምቱ የዝውውር መስኮት የታገደና ከፌዴሬሽኑ
ጽ/ቤት ምንም አይነት ግልጋሎት የማያገኝ መሆኑ ታውቋል። የፋሲል ከነማ አመራሮች በውሳኔው ደሰተኛ ካልሆኑ ወደ ካስ “የዓለም አቀፉ የእግርኳስ የግልግል ፍርድ ቤት” ጉዳዩን የመውሰድ የመጨረሻ እድል ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።