*…የጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት ይጠበቃል…
*…ፋሲል ከነማ ቅሬታውን በደብዳቤ ገልጿል…
*….የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ነገ ጠዋት 4 ሰዓት
ይሰበሰባል…
*…በተቀጡት ዳኞች ምትክ ሁለት ዳኞች ተተክተዋል
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት ሲካሄዱ ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ከአዳጊው አዲስ አበባ ከተማ ጋር 2ለ2 ተለያይተዋል።
ይህን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት የመራው በዘንድሮ የውድድር አመት ሁለተኛው ጨዋታ የሆነው ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ሲሆን ለአዲስ አበባ ከተማ የሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት ስህተት በመሆኑ ውሳኔው 2 ለ 1 የማሸነፍ ዕድል የነበራቸውን አጼዎቹን አቀሳጭቷል።
የዚህን ጨዋታ መጠናቀቅን ተከትሎ ውሳኔው ስህተት መሆኑ የገባው አርቢትሩ ፋሲል ከነማ መልበሻ ቤት ገብቶ ተጨዋቾቹን ይቅርታ ጠይቋል። ስህተት መስራቱን አምኖ አውቆ የሰራው ስህተት አለመሆኑን በመግለጽ ይቅርታውን እንዲቀበሉት ተማጽኗል። ይቅርታው በእኛ ሀገር ያልተለመደ ቢሆንም ስህተቱን ማመኑ ሙያውን እንደሚያከብር ያሳያል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ያም ሆኖ ፋሲል ከነማ የዳኛውን ይቅርታ መጠየቅ አካቶ ለሊግ ኩባንያው የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱ ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታው ኮሚሽነር አዲሱ ነጋሽ ሪፖርት የሚጠብቀው የብሄራዊ የዳኞች ኮሚቴ በአምላክ ካለው ስምና ዝና አንጻር ዝምታን ይመርጣል?ወይስ ሌሎች ዳኞች ላይ የሰነዘረውን የቅጣት በትር ያሳርፍበታል? የሚለው የስፖርት ቤተሰቡን ጉጉት አንሮታል። አርቢትሩም በኮሚቴው ውሳኔ ከአዳማ መመለሱ የታወቀ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ብቃትና ተቀባይነት በሀገር ውስጥ አለመደገሙ መነጋገሪያ ሆኗል። ሊግ ኩባንያው 19ኛው ሳምንት ስምንት ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነገ ጠዋት አራት ሰአት ላይ የሳምንቱን ጨዋታ ገምግሞ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጨዋታ ኮሚሽነሩ 6.5 ነጥብ በማግኘታቸው ዕገዳ የተላለፈባቸው አርቢትሮችን የሚተኩ አርቢትሮች ታውቀዋል። በዚህ መሠረት ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩን ፌዴራል አርቢትር ሀብታሙ መንግስቴ ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር ተመስገን ሳሙኤልን ፌዴራል ረዳት ዳኛ ክንፈ ይልማ እንዲተኳቸው መደረጉ ታውቋል።
ከዚሁ ከዳኛ ኮሚቴ ሳንወጣ ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ የሚሰጠው ውሳኔ ምስጢር እያፈተለከ ሲሆን አባላቱ መሃል መከፋፈል እየታየም ነው። የኮሚቴው ሰብሳቢ ከዳኝነት ጋር ዕውቀት የሌላቸው ስራ አስፈጻሚው አቶ ኢብራሂም መሀመድ የተቀጣውን ኢንተርናሽናል አርቢትሮ ቴዎድሮስ ምትኩን አትምጣ እዚያው አዳማ ቆይ ማለታቸው የተሰማ ሲሆን አንዳንድ የኮሚቴው አባላት ውሳኔያቸው ቅሬታ ሲበዛባበት አልነበርንም ውሳኔውን አናውቀውም በማለት ሲሸሹና ተደብቀው ለማለፍ ሲሞክሩ መታየታቸው ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አርቢትር “ብሄራዊ የዳኞች ኮሚቴ ውስጥ እያሉ ውሳኔ ሲተላለፍ አናውቀውም እያሉ የጎን ወሬ ማስወራታቸውን ማቆም አለባቸው የለሁበትም አላውቅም ማለት ከተጠያቂነት አያተርፋቸውም ከጀርባችን ተንኮል ይሰራል ካሉ ጉዳዩን ይፋ አድርገው ጥፋተኛውን ማጋለጥ እንጂ ተደብቆ ጣት በመጠቆም መቆየት አያዋጣም” ሲሉ ይመክራሉ።