የአሠልጣኝ ዘርአይ ሙሉው ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ 8 ጨዋታዎች 3 ጊዜ አሸንፎ 1 ጊዜ አቻ ወጥቶ 4 ጊዜ ተሸንፎ በ10 ነጥቦችና 4 የግብ እዳ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ በሲዳማ ቡና ክለብ የቅርብ አመታት ታሪክ ላይ ያልተከሰተ ውጤት መነጋጋሪያነት ፈጥሯል፡፡ በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ዛሬ ከቀኑ ዛሬ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚጫወተው የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር መሪ ፈቱዲን ጀማል ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ከጊዮርጊስ ጋር ስላላቸው ጨዋታና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- የጅማ ከተማ ቆይታችሁን እንዴት አገኘኸው?
ፈቱዲን፡- የጅማ ቆይታችንማ ብዙ ፈታኝ ነገሮች አሉበት በተለይ ሜዳው አስቸጋሪ ነበር ልምምድ የሚሰራው ተራ በተራ ነው አንዱ ክለብ ሲጨርስ ሌላው በተራ ነው ልምምድ ሲሰራ የነበረው…. የጨዋታው ሜዳም እንዲያችሁት በጣም ፈታኝ ነበር፤ ለውድድሩ ይመጥናል ብዬ የማላስበው ሜዳ ነው የሆነብን… ተደራራቢ ጨዋታዎች ሲደረጉበት የባሰ ፈትኖናል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- የሊጉን ፉክክር እንዴት ገመገምከው?
ፈቱዲን፡- 13 ቡድኖች እንደመሆናቸው ላለመውረድና ወደላይ ለመውጣት የሚደረገው ፉክክር ጠንከር ያለ ሆኖብኛል፡፡ ከሌላው ጊዜ የተለየ ፍልሚያ እየታየ ነው ከ13 ክለቦች 3 ወራጅ መሆናቸው ጠንካራ ትግል እንድናደርግ እያደረገን ነው ሲጀምር ጥሩ ያልነበሩ ቡድኖች እየተስተካከሉ መጥተዋል ግጥሚያዎቹንም ፈታኝ አድርገዋቸዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በ9ኙ ሳምንት ምርጥ የምትለው ቡድን አይተሃል?
ፈቱዲን፡-ብዙ ታዳጊዎች ከታች ወጥተው መታየት የቻሉበት ውድድር ሆኗል፤ የተለየብኝ ይሄኛው አጋጣሚ ነው፤ እንደቡድን ካየን ልዩነት ይፈጥራሉ የተባሉ ቡድኖች ደከም ሲሉ ይህን ያህል ጠንካራ ተፎካካሪ አይሆኑም የተባሉ ክለቦች ደግሞ በርትተው የታዩበት ውድድር መሆኑንም ታዝቤያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡናን እንዴት አየኸው? በ9 ጨዋታ 10 ነጥብና 4 የግብ እዳ መያዙ ምን ስሜት ፈጠረ?
ፈቱዲን፡- ያለንብት ደረጃ ሲታይ ለሲዳማ ቡና አዲስ ነው ከዚህ በፊት አናውቀውም ነገር ግን የጎዳን የመጀመሪያ ሳምንት የአዲስ አበባ ስታዲየም ግጥሚያዎች ላይ የጣልናቸው ነጥቦች ናቸው፤ ሜዳው ለኛ ለየት ብሎብናል የተዘጋጀነውና ልምምድ የሠራነው በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ስለሆነ ጥሩ ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል… ይሄ ነው የጎዳን ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ዳኝነቱስ እንዴት አገኘኸው?
ፈቱዲን፡- የዘንድሮ ዳኝነት ብዙ ውዝግቦች የተፈጠሩበት ነው ብዬ አስባለሁ፤ አንዳንድ ያልጠበቅናቸው አሁን የመጡ ዳኞች ጥሩ ብቃት አሳይተውናል አብዛኛው ስህተት እየተፈጠረ ያለው ረዳት ዳኞች ዙሪያ ነው ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የተወሰኑ ስህተቶችን እያየን ነበር ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶች ቢስተካከሉ ጥሩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከሜዳው ውጪ የክለባችሁ ችግር ምንድነው..?
ፈቱዲን፡-የሜዳው ችግር ነው በዛ ሜዳ ላይ ባንሰራ የተሻለ ስራ እንሰራ ነበር ብዬ አምናለሁ… የመጀመሪያ ሳምንታት ጨዋታዎች ጎድተውናል በመጀመሪያ ሣምንት ነጥቦችን ከጣልክ ደግሞ ለማገገም ይከብዳል ጅማ ከመጣን በኋላ 3 ጨዋታዎችን አድርገን 2 ረትተን 1 ተሸንፈናል በርግጥ ጫናዎች ቢኖሩም የመሻሻል ሁኔታዎች ታይተዋል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- የጅማ ሜዳ ከአዲስ አበባ ስታዲየም የባሰ ቢሆንም እዚህ ጥሩ ውጤት መያዛችሁ ሌላ ችግር እንደነበር አያሳይም?
ፈቱዲን፡- /ሳቅ/ ብዙ የሳር ሜዳዎችን አልለመድንም ነበር ነገር ግን ግዴታ ውስጥ ገብተን ለመጫወት ችለናል ሜዳው ለጥሩ ጨዋታ አይታሰብም ኳስ ይዘው የሚጫወቱ ቡድኖች ተቸግረዋል እኛም የግድ ሆኖ ወደ ፕላን ቢ አጨዋወት በመግባታችን ነው ተጠቃሚ የሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- የተከላካይ ክፍሉስ ደካማ አልሆነም?
ፈቱዲን፡- አዎ አዲስ አበባ ስታዲየም የተቆጠሩብን በርካታ ግቦች ጎድተውናል ዋጋም አስከፍለውናል በሂደት ግን ተከላካይ ክፍሉም ሆነ ሙሉ ቡድኑ እየተስተካከለ ሲመጣ ይሄ ችግር ይወገዳል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡና ጥሩ አለመሆኑን ስታይ ምነው ድጋሚ ባልፈረምኩ አላልክም?
ፈቱዲን፡- /ሳቅ/ እንዲህ እንኳን አላስብኩም ቡድኑን ስታይ ያለው ነገር እንደሚስተካከል ያስታውቃል፤ አስፈሪ የሆነ ችግርም የለብንም አሰልጣኙ ሊጠቀምባቸው ያስፈረማቸው ተጨዋቾች እንደነ ጫላ አይነቱ ሲመለሱ የተሻለ አቋም ይኖረናል ጥሩ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በወቅታዊ አቋምህ ደስተኛ ነህ? ወይስ ምርጡን ፈቱዲንን ከፊታችን ባሉት ጨዋታዎች እንጠብቅ?
ፈቱዲን፡- ያው አንድ ቡድን ውስጥ ያለው አቋም በደረጃው ቀጣይነት ከሌላው ጥሩ የሚጫወት ተጨዋች ቀዝቀዝ ብሎ ሊታይ ይችል ይሆናል… በእርግጥ እኔንም እንዳየኸኝ ከመጀመሪያው ጨዋታዎች ጅማ ላይ በነበሩት ጨዋታዎች የተሻለ ነገር አሳይቻለሁ.. በቀጣይ ግን አቋሜን በተሻለ መልኩ አስተካክዬ ቡድኑን መጥቀም እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በደጋፊ አለመታጀባችሁ የተወሰነ የሚቀንሰው ነገር የለም?
ፈቱዲን፡- ያለ ደጋፊ መጫወት የተወሰነ ጉዳት ይኖረዋል በደጋፊ የተለመደ ኳስ ያለ ደጋፊ ሲሆን መቀዝቀዝ ሊታይ ይችላል ግን ወደፊትም ያለደጋፊ የሚካሄድ ውድድር ሊኖር ስለሚችል ያለ ደጋፊ መጫወትን መልመድ የግድ ይላል፡፡
ሀትሪክ፡- በዲ.ኤስ.ቲ.ቪ መተላለፉ ራሱን የቻለ ጥቅም ይኖረዋል አይደል?
ፈቱዲን፡- አዎ ትልቅ ነገር ነው ደጋፊዎች ዲ.ኤስ.ቲ.ቪ ቤት ገብተው ነው የቡድናቸውን ጨዋታ የሚከታተሉት ያም ቢሆን ጥሩ ነገሩ ሁላችንም ችግራችንን ደጋግመን አይተን ለማረም ያሉንን ጥሩ ነገሮች ለማስቀጥል ዲ.ኤስ.ቲ.ቪ ትልቅ ጥቅም አለው፤ ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኞች የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች በዲ.ኤስ.ቲ.ቪ አይተው እንጂ ሰው ጠይቀው የሚያስፈርሙበት ጊዜ ያለፈ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዳሜ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃችኋል… ምን ውጤት ይጠበቃል /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ሀሙስ ምሽት ነው/?
ፈቱዲን፡-እነርሱም በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ አልነበሩም እኛም አሁን ብንሻሻልም በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ አልነበርንም በጨዋታው ሁለታችንም ውጤቱን እንፈልገዋለን ጠንካራ ፍልሚያ ይሆናል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን የማሸነፍ አቅም አለን እያልክ ነው?
ፈቱዲን፡- አዎ ብዙ ሰው ሲዳማ ጥሩ አይደለምና ጊዮርጊስን አያሸንፍም ብሎ ያስባል ነገር ግን ካለን አቅምና ካለፉት ጨዋታዎቻችን አንፃር ሳየው ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈን ወደ ሚጠበቀው ደረጃችን ከፍ እንላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ጊዮርጊስን ብቻ ሣይሆን ሌሎች ግጥሚያዎችንም ረተን ወደ ላይ እንደምንጠጋ ርግጠኛ ነኝ ለሁሉም ቡድን ተመሳሳይ ዝግጅት አደርገን ነው ለጨዋታው የምንዘጋጀው፡፡
ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ጫና ይፈጥርብናል ለነርሱ ማስፈራርያ ነው የምትለው ተጨዋች ማነው?
ፈቱዲን፡- ጊዮርጊስ ጠንካራ ቡድን መሆኑ ይታወቃል ዘንድሮ ደግሞ ከወገብ በላይ ያለው ብዙ ነገር ማድረግ የሚችሉ ልጆች የተሰባሰቡበት ቡድን ነውና እገሌ ብለህ ለይተህ የምትጠራው ሳይሆን ሁላቸውም አደጋ መፍጠር የሚችሉ መሆናቸው ይታወቃል.. ያም ቢሆን እኛም በጥንቃቄ ስለምንጫወት ያሸነፉናል ብዬ አላምንም በደንብ ተዘጋጀተን የምንጫወት ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- አዲስ ግደይ የሲዳማ ቡና ምልክት ነበር… ቅዳሜ ደግሞ በተቃራኒነት ሊገጥማችሁ ነውና የምትለው ነገር አለ?
ፈቱዲን፡-አዲስ በሲዳማ ቡና ውጤታማ ቆይታ እንደነበረው ይታወቃል፤ እንደ ወንድምም እንደ ጓደኛም መልካም ነገር እመኝለታለሁ ነገር ግን አሁን ተፋላሚ ነውና ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ብንወድህም ከኛ ጋር ስትጫወት አይሳካልህም እያልከው ነው?
ፈቱዲን፡- /ሳቅ በሳቅ/ እሱንማ አላህ ነው የሚያውቀው፤
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ጥያቄ… ከትዳር መመስረት በኋላ ረዘም ያለ እረፍት ሳይኖርህ ወዲያውኑ ወደ ዝግጅት የገባኸውና ከባለቤትህ ጋር አልከበዳችሁም?
ፈቱዲን፡-/ሳቅ/ አዎ ከበድ ይላል እርሷም የመጣችው ከውጪ በመሆኑ ብዙ ጊዜ አልነበረንም በቀጥታ ነው ወደ ዝግጅት የገባሁት ምንም ነገር ማድረግ አልቻልንም… አንዳንዴ ነገሮች አልጋ በአልጋ ላይሆኑ ይችላሉ ቢከብደንም ተማምነን ቅድሚያ መስጠት ላለብን ስራ ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡ በቅርቡም ከተወሰነ ጊዜያት በኋላ ወደ ውጪ ትመለሳለች እንዳልከው የዕረፍት ጊዜ ብዙ ሳይኖረን መቅረቱ ይከብዳል ነገር ግን ችለነዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ አይደለም ኧረ ናፍቃው ከሆነ ሚስቱን ይመልከትም ይባላልኮ?
ፈቱዲን፡-/ሳቅ በሳቅ/ ኢትዮጵያ ውስጥኮ የሚያያዘው ከእንደዚህ አይነት ነገር ጋር ነው /ሳቅ/
ሀትሪክ፡- አመሰግናለሁ፡፡