*….. በርካታ ዳኞች የአካል ብቃት ፈተና መውደቃቸው
ተነግሯል…
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ በዘንድሮው የውድድር አመት የፊፋን ባጅ ለማግኘት በክፍት ቦታዎች ላይ የሚገቡ አርቢትሪችን ይፋ አድርጓል።
እንደ ኮሚቴው መረጃ በወንዶች ዋና ዳኛ 96.034 ከመቶ ውጤት ያገኘው ፌዴራል አርቢቢትር ኤፍሬም ደበሌ፣በሴቶች ደግሞ 96. 545 ያመጣችው ፌዴራል አርቢትር ማርታ መለሰ ፣ በወንዶች ረዳት ዳኝነት ኮታ ከመቶ 96.985 ነጥብ ያገኘው ሲራጅ ኑርበገንና
95.656 ያገኘው አሸብር ታፈሰ እጩ ኢንተርናሽናል ዋናና ረዳት ዳኞች ተብለው ለፊፋ ስማቸው ተልኳል። በረዳት ቦታው ግን ያለን ኮታ 6 በመሆኑ የአሸብር ታፈሰ ባጅ የማግኘት እድሉ የጠበበ መሆኑ ተገምቷል።
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዳኞች ኮሚቴ ባገኘው ዝርዝር መሰረት ያቀረባቸውን እጩ ኢንተርናሽናል ዳኞች የፊፋ ዳኞች ኮሚቴ ገምግሞ ከተቀበላቸው የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል አርቢትርነት በወንዶች 7 ዋና ዳኞችና 7 ረዳት ዳኞች በሴቶች 4 ዋና ዳኞችና 4 ረዳት ዳኞች ኮታ እንዳላት ይታወቃል።
በሌላ በኩል ለ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳኞች የአካል ብቃት ፈተና ሲሰጥ በርካታ ዳኞች መውደቃቸው ተሰማ።
ከተሰጠው ኩፐር ቴስቱ አስቀድሞ በተሻሻሉ የእግርኳስ ህጎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ በተሰጠ የኩፐር ቴስት 40 ዋናና 52 ረዳት ዳኞች የተፈተኑ ሲሆን ከ40 ዎቹ ዋና ዳኞች 28 ዳኞች ሲያልፉ 12ዳኞች ወድቀዋል። ከ52 ረዳት ዳኞች ደግሞ 36 ረዳት ዳኞች ፈተናውን ወድቀዋል።
በ2016 የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚያጫውቱ ሴት ዳኞችም የአካል ብቃት ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን 18 ዋናና 40 ረዳት ዳኞች ፈተናውን ወስደው 4 ዋናና 9 ረዳት ዳኞች ብቻ አልፈዋል። 14 ዋናና 31 ረዳት ዳኞች ፈተናውን መውደቃቸው ግርምትን ፈጥሯል።
በዚህ ፈተና ላይ ከተካፈሉት ዳኞች መሃል የ2016 ኮከብ ዳኛው ፌዴራል አርቢትር ቢኒያም ወ/አገኘሁን ጨምሮ ኢንተርናሽናል አርቢትር ለማ ና የዛሬውን የሲቲ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሆነውን የሀድያ ሆሳዕናና የኢትዮጵያ መድን ጨዋታን የመራው ፌዴራል አርቢትር ሚካኤል ጣዕመ በጉዳት አቋርጠው ሲወጡ ፌዴራል ረዳት ዳኛ ሻረው ጌታቸው በቀይ ካርድ መባረሩ ታውቋል። ከሰሞኑ ብሄራዊ ስፖርት አካዳሚ የተሰጠውን የአካል ብቃት ፈተና በሴት ኢንተርናሽናል ዋናና ረዳት ዳኞቹ በሙሉ ማለፋቸው ታውቋል።
የፊፋ ባጅ እንዲያገኙ በተላኩ ዳኞችና ስማቸው መላክ ነበረበት በተባሉ ዳኞች ዙሪያ የተነሱ ልዩነቶች ዙሪያ በቀጣይ በሌላ መረጃ እንገናኛለን።