የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በኢሲኤ አዳራሽ አከናውኗል ።
መርሀግብሩ ምልዐተ ጉባዔው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ የመክፈቻ የእንኳን ደህኔ መጣችሁ ንግግር በኋላ የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትርሩ አት ቀጀላ መርዳሳ ንግግር አድርገዋል ።
በመቀጠልም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የዕለቱን አጀንዳዎች ለተሰብሳቢዎቹ አቅርበዋል ። አጅንዳዎቹም በአቶ ኃይሉ ሞላ አማካኝነት ማብራርያዎች ተሰጥተውባቸዋል ። ከአቶ ኃይሉ ማብራሪያዎች በኋላ ከጉባኤው አባላት ጥያቄዎች እና ምክረሀሳቦች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በቅድሚያ የቀረበው የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ አመራር ደንብ ማሻሻያ ሲሆን ከገለፃው እና ከውይይቱ በኋላ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል ።
በመቀጠል የቀረበው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን በዚህ አጀንዳ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበት በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል ። ቀጥሎ የቀረበው የተሻሻለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማስፈፀሚያ ደንብ ረቂቅ ቀርቦ በተመሳሳይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአባላጫ ድምፅ ፀድቋል ።
አጀንዳዎችን የማፅደቅ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የምርጫ አስፈፃሚ እና የይግባኝ ሰሚ እጩዎች ቀርበው ድምፅ ተሰጥቶባቸዋል ። በምርጫ አስፈፃሚ በቅድሚያ ከቀረቡት ስምንት ግለሰቦች እና በኋላ ላይ ከተጨመሩት ወይዘሮ ረሂማ ዐወል መካከል 5 አባላት የተመረጡ ሲሆን ወይዘሮ ረሂማ ዐወል ፤ አቶ ኃይሉ ሞላ ፤ አቶ ኢሳይያስ ደንድር ፤ አቶ መንግስቱ ማሩ እና አቶ በለጠ ዘውዴ በኮሚቴው ውስጥ ሲካተቱ አቶ ኢብራሂም አደም እና አቶ አበባው ሰለሞን በተጠባባቂነት ተይዘዋል ። በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ እጩ ከነበሩት አምስት አባላት መካከል አቶ አንበሳው እንየው ፤ አቶ ብርሀኑ ከበደ እና አቶ ተስፋዬ ዘውዴ በተሰጣቸው ድምፅ የኮሚቴው አባላት ሆነው የተመረጡ ሲሆን አቶ አፈወርቅ አየለ እና አቶ መኮንን ጤናው በተጠባባቂነት ተካተዋል ።
በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ የመዝጊያ ንግግር ካደረጉ በኋላ አስቸኳይ ጉባዔው ተጠናቋል ።