ምሽት ላይ የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የመቻል ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሰባተኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ በማድረግ የገቡ ሲሆን ባህሩ ነጋሽን በቻርለሽ ሉክዋጎ ምትክ ተክተቃል ። በመቻል በኩል ደግሞ በስድስተኛው ሳምንተሰ በወላይታ ድቻ በተረተቡት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራ አንድ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ በግርማ ዲሳሳ እና ከነአን ማርክነህ ምትክ ፍፁም አለሙን እና በረከት ደሰታን አሰልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ ጥረቶች ቢታዩም ቀስ በቀስ ፈረሰኞቹ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል ።
ምንም እንኳን ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወስዱም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ደካማ ነበሩ ። በአንፃሩ በመቻል በኩል የተጋጣሚን የኳስ ፍሰት በማቋረጥ የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በማድረስ በተሻለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በነዚህ ደቂቃዎች ላይ መቻሎች በግሩም ሀጎስ እና ከነአን ማርክነህ አማካኝነት ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ኳሶቹ ኢላማዎች ባለመጠበቃቸው ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ።
በ18ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ቀዳሚ የግብ ሙከራቸውን አድርገዋል ። ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም የመቻሉ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ጨዋታው በተመሳሳይ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ሻምፕየኖቹ መሪ መሆን የሚችሉበትን ዕድል 42ኛው ደቂቃ ላይ አስመልክቶናል ። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቢንያም በላይ ጋር በአንድ ሁለት ቅብበል ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ነው ሳይጠቀምበት የቀረው ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፈረሰኞቹ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነታቸው ቀጥለው የነበረ ቢሆንም የማጥቃት ሶስተኛው ዞን ላይ የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ጥረቶቻቸው በግብም ሆነ በግብ ሙከራ እንዳይታጀቡ አድርጓቸዋል ።
በመቻል በኩል የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን የመጠቀም የመጀመሪያ አጋማሽ ፍላጎት በሁለተኛው አጋማሽም ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም ባሆሩ ነጋሽን የፈተኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ቆይተዋል ።
በ49ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የቅጣት ምት ሱሌማን ሀሚድ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን አሻግሮ ከነአን ማርክነህ ኳሱን ለማውጣት ሲሞክር ለጥቂት ራሱ ላይ አስቆጥሮ ነበር ።
መቻሎች በቀጣይ አከታትለው ሁለት የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ኢላማቸውን ግን የጠበቁ አልነበሩም ።
ቀዳሚው የሳሙኤል ሳሊሶ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻምቶ በግብ ጠባቂው የተመለሰውነሰ ኳስ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል ። በ70ኛው ደቂቃ ላይም በረከት ደስታም በበኩሉ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ባህሩን የፈተነ አልበረም ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይ በፈረሰኞቹ በኩል ከቅጣት ምት ወደ ግብ የተሻገረውን ኳስ የመቻል ተጫዋቾች በአግባቡ ከግብ ክልል ሳያርቁ በመቅረታቸው አቤች ያለው አግኝቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በመጨረሻም ጨዋታው ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ህዳር 13(ማክሰኞ) ቀን 10:00 ላይ መቻል ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በዕለቱ ምሸት 1:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል ።