በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ከላይ የተቀመጡትን ክለቦች ባገናኘው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ መድኅንን 2 ለ 1 አሸንፏል ።
በጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ15ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን በማድረግ ሄኖክ አዱኛ ፣ ምኞት ደበበን እና ቸርነት ጉግሳን በሱሌማን ሀሚድ ፣ በአማኑኤል ተርፉ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ተክተው ገብተዋል ።
በኢትዮጵያ መድኅነ በኩል በተመሳሳይ በሳምንቱ ሀድያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሶሰት ለውጦችን በማድረግ ቻላቸው መንበሩ ፣ ዮናስ ገረመው እና ብሩክ ሙሉጌታን በአብዱልከሪም መሀመድ ፣ አሚር ሙደሲር እና ሐቢብ ከማል ምትክ አሰልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ተጋጣሚ ግብ ለመድረስ ፍላጎቶች የታዩባቸው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮጵያ መድኅን በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ኳስን ከኋላ መስርተው እንዳይወጡ በማድረግ እና ጫናዎችን በመፍጠር የተሻለ ለመንቀሳቀስ ችለዋል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከኋላ መስርተው ለመውጣት ተቸግረው የቆዩ ሲሆን በተለይም ለቡድኑ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ እስማኤልም ኦሮ አጎሮ ኳሶችን ከማድረስ አንፃር ደካማ አጋማሽ አጋማሽ አሳልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያው የግብ ሙከራ የታየው 21ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። በአጋጣሚው ሀብታሙ ሸዋለም ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ አግኝቶ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ቻርለስ ሉክዋጎ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ይህ ኳስ በፈጣን ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ መድኅን የግብ ክልል ሲደርስ አቤል ያለው በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ አቡበከር ኑራ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ መድኅን ወደ ፊት በመደረሱ ረገድ ከተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ ሆነው ታይተዋል ።
የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ሀይሌው ቡድን ምንም እንኳን የተሻለ የማጥቃት ጫና መፍጠር ቢችልም ኪቲካ ጀማ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ሆኖ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ የግብ ሙከራ ውጪ ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ዕድል አልፈጠሩም ።
በተሻለ መነቃቃት የተጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያው ግብ በኢትዮጵያ መድኅን በኩል ተቆጥሯል ።
በረጅም የተሻገረውን ኳስ በቀኝ መስመር አቅጣጫ ላይ የነበረው ኪቲካ ጀማ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ምኞት ደበበ ለማውጣት መቸገሩን ተከትሎ ሳይመን ፒተር ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በፍጥነት መልስ ለመስጠት መንቀሳቀስ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወድያውኑ በቢንያም በላይ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ያደረጉት የግብ ሙከራ በአቡበከር ኑራ ግብ ከመሆን ድኗል ።
የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና የፈጠሩት ፈረሰኞቹ በ64ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል ። ቢንያም በላይ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከመረብ ላይ አሳርፏል ።
የጨዋታው ውጤት ወደ አቻ ከተቀየረ በኋላ በሁለቱም በኩል በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድረገዋል ። በዚህ ሂደት ያሰቡትን ያሳኩት የአምና ሻምፕየኖቹ ፈረሰኞቹ ናቸው ።
ሀብታሙ ሸዋለም በረጅም ወደ ፊት ለማሻገር የመታው ኳስ ባሲሩ ዑመርን መቶት ሲመለስ ያገኘው ግብ አዳኙ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በቀጥታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምትተ በአቡበከር ኑራ መረብ ላይ ኳሱን አሳርፏል ። ይህንንም ተከትሎ ኦሮ አጎሮ በውድድር ዓመቱ በ16 ጨዋታ ያስቆጠረው 16ኛ ግቡን ሆኖ ተመዝግቧል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቤል ያለው በረጅም የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ሶስተኛውን ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የመጀመሪያ የኳስ ንክኪው ልክ አለመሆኑን ተከትሎ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ መድኅኖች በተሻለ የቅዱስ ጊዮርጊሰን የኋላ መስመር ለመፈተን ችለው ነበር ።
በ76ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለም ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሀቢብ መሀመድ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በቻርለስ ሉክዋጎ ተመልሷል ።
በተጨማሪም ተከልኝ ደጀኔ በ81ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ የመለሰበት ኳስ እና በ86ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማ ሶስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን አልፎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ኳሱ ከግብ አናት በላይ በመውጣቱ ሳይሳካ ቀርቷል ።
በመጨረሻም በ90+5 ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማ ከቅጣት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በቻርለስ ሉክዋጎ የተመለሰበት ሙከራ የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ሙከራ ሆኗል ። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 1 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል ።
ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 35 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር ኢትዮጵያ መድኅን በ31 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መጋቢት 3(ዕሁድ) ምሸት 1:00 ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ መጋቢት 5(ማክሰኞ) ቀን 10:00 ላይ ኢትዮጵያ መድኅን አርባምንጭ ከተማን የሚገጥም ይሆናል ።