በሊጉ የሶስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት መርሀግብሮች ቀን ሰባት ሰዓት ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 1 ረቷል ።
ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት ከለገጣፎ ለገዳዲ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ አቤል አሰበ እና ያሬድ ታደሰን በብሩክ ቃልቦሬ እና ዮሴፍ ዮሐንስ ምትክ ሲያሰልፉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ በሳምንቱ ሲዳማ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ አያኖ ፒፕ ፤ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ፤ ራምኬል ሎክን በማሳረፍ መሳይ አያኖ ፤ ስቲቨኝ ናያርኮ እና ሪችሞንድ አዶንጎን አሰልፈዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም በተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ ኳሱን በመያዝ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ በተለይም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በ20ኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን መሀመድ አብዱለጢፍ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ድሬዳዋ ከተማዎች የሀድያ ሆሳዕናን የኳስ ሂደት በማቋረጥ ያገኙትን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ወደ ግብ ቢልከውም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ቀዳሚውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። ባዬ ገዛኸኝ በረጅም የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሲያሻግረው ተከላካዩ አሳንቲ ጎድፍሪ በግንባር ገጭቶ ለማውጣት ሲሞክር ከግብ ጠባቂው ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ኳሱ የደረሰው ስቲቨን ንያርኮ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ አስቆጥሯል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሀድና ሆሳዕናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በዚህም 42ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ።
በአጋጣሚው አቤል አሰበ ወደ ግብ ክልል በአየር ያሻገረውን ኳስ ቻርለስ ሙሱጌ ተቆጣጥሮ ከመረብ አሳርፎታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ዳግም መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ብሩክ ማርቆስ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ግርማ በቀለ በግንባር በመግጨት በፍሬው ጌታሁን መረብ ላይ አሳርፎታል ።
ዳግም መሪነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ይበልጥ አጥቅተው መጫወት የቀጠሉት ነብሮቹ በ54 እና 59ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ።
በቀዳሚው ሙከራ ግርማ በቀለ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ በግንባር ገጭቶ ኳሱ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ሲሆን ከአምሰት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ስቲቨን ኒያርኮ ያገኘውን የግብ ሙከራ ፍሬው ጌታሁን ተቆጣጥሮታል ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ለውጦችን በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም በ66ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ተሻግሮ መሳይ አያኖ ግብ ከመሆን ካዳነው ኳሽ ውጪ ሌላ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ።
ይባስ ብሎም መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ ሶስተኛ ግብ አስተናግደዋል ።
በመልሶ ማጥቃቶ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል የደረሰውን ኳስ ተቀይሮ የገባው መለስ ሚሻሞ ከባዬ ገዛኸኝ ተቀብሎ ከመረብ አሳርፎታል ። በመጨረሻም ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና የ3 ለ 1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጨው ጥቅምት 4(ረቡዕ) 7:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ከተማ ሲጫወት ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ቀን 10:00 ላይ ባህርዳር ከተማን ይገጥማል ።