ከደረቅ ቼክ ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ የዋሉት የሀድያ ሆሳዕናው የፋይናንስ ሃላፊ ከተከሰሱበት 11 ክሶች በ10ሩ ክሶች የፊታችን ቅዳሜና ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተባለ።
ሀላፊው ለ15 ተጨዋቾች የደረቅ ቼክ ሰጥተዋል በሚል በ11 ክስ ተከሰው ትላንት አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው በአንዱ ተጨዋች የ120 ሺህ ብር ክስ በ4 ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ቢወሰንም በ10ሩ ክስ ወደ ማረፊያ ቤት እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል። በተመሳሳይ ክስ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ በፖሊስ እየተፈለጉ ሲሆን ስለሁኔታው ለማጣራት በግል ስልካቸው ላይ ቢደወልም ዝግ በመሆኑ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
በእግር ኳሱ የፍትህ አካላት ተቀባይነት ያጣው የክለቡ አመራሮች ክስ በመደበኛ የፍትህ ስርአትም መሸነፉን የሚያሳይ ሲሆን አሁን በደረሰው አዲስ መረጃ መሰረት የአዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ውል ማጸደቅ አለመቻላቸውና የስራ ባልደረባቸው መታሰሩን የተረዱት የክለቡ የቦርድ አባላት ሙሉ የሆነ ተግባራዊ ምላሽና ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ወይም ነገ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተነግሯል።